የበሰቃ ሃይቅ ከስጋትነት ወደ ልማት አማራጭነት እየተሸጋገረ ነው

117

ግንቦት 7/2011 በፍጥነት እየተስፋፋ በመምጣት የመተሀራ ከተማ የህልውና ስጋት ሆኖ የቆየውን የበሰቃ ሀይቅ ወደ ልማት ለማሸጋገር የተጀመረው ጥረት ውጤታማ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ገለፁ ።

የመተሀራ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ በበኩላቸው በሀይቁ ዙሪያ የነበረው ስጋት በመቃለሉ ባለሃብቶች ወደ አካባቢው መጥተው ልማታዊ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል ።

ሃይቁ በ1966 ዓ.ም በትንሽ ቦታ መፍለቅ እንደጀመረና ባለፉት 45 ዓመታት በፍጥነት በመስፋፋት በነዋሪዎቹ ዘንድ ከተማዋን ሊያጥለቀልቃት ይችላል የሚል ስጋት አሳድሮ መቆየቱን ከከተማው የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል ።

በፅህፈት ቤቱ የኮሙኒኬሽን ባለሙያ አቶ ገዛሊ ሀሰን እንደገለጹ ሀይቁ እስከ 2004 ዓ.ም. በነበረው ጊዜ 1ሺህ 278 ሔክታር መሬት በመሸፈን የወጣቶች ማእከል ፣ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፣ጤና ጥበቃ ፅህፈት ቤት ፣ የከብት ማድለቢያዎች ፣ የመንግስትና የግል መኖሪያ ቤቶችን በማፈራረስ በርካቶችን አፈናቅሏል።

አሁን ግን የውሃ መውረጃ ቦይ ተከፍቶለት ወደ አዋሽ ወንዝ በማቀላቀል እንዲተነፍስ በመደረጉ የከተማው ስጋት መቃለሉን ተናግረዋል ።

የመተሀራ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ ሃልኮ ፈንታሌ በበኩላቸው የበሰቃ ሀይቅ በርካቶችን ያፈናቀለና ወደ ከተማዋ በመጠጋት ስጋት ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ወደ አዋሽ ወንዝ በማስተንፈስ ህዝቡ እፎይታ ማግኘቱን አስረድተዋል ።

በአካባቢው ለ600 ሰዎች የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታና ካርታና ፕላን ተሰጥቶ እንደነበርና በሀይቁ መስፋፋት ምክንያት አካባቢው በውሃ በመጠቃቱ መስተጓጎሉን ከንቲባዋ ተናግረዋል ። 

በበሰቃ ወንዝ ይጠቃል ተብሎ ይሰጋ የነበረው ቀጠና 6 በተባለው አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎችን ከቦታው ለማስነሳት የነበረው እቅድም አሁን በተፈጠረው የሃይቁ አንፃራዊ መቀነስ ምክንያት ባሉበት እንዲቆዩና ተረጋግተው መደበኛ ኑሮአቸውን እንዲመሩ ተደርጓል”ብለዋል ።

ሀይቁ በአሁኑ ወቅት ከስጋት ተላቆ የከተማዋ ውበትና የልማት ምንጭ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የገለፁት ከንቲባዋ ባለሃብቶች በሀይቁ ዙሪያ የመዝናኛ ማእከላትን በመገንባት ለቱሪዝም እድገት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል ።

በመተሀራ ከተማ 02 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ውብሸት መስፍን በሰጡት አስተያየት በአሁኑ ወቅት በመንግስት እገዛ ነዋሪው ከበሰቃ ወንዝ ስጋት እፎይታ አግኝቷል ።

ሐይቁ መተንፈሻ ስለተሰራለት ከክረምት በስተቀር በበጋ ወራት የሚያሰጋ ነገር አለመኖሩን አቶ ውብሸት ገልፀው እንዲያውም ቀጤማ ማብቀል መጀመሩን ፣ ዓሳና አዞ በስፋት የሚታዩበት መሆኑን ገልፀዋል ።

የበሰቃ ሀይቅ በአግባቡ ከለማ እንደ ሀዋሳና ባህርዳር መተሃራን ሳቢ የመዝናኛ ከተማ ማድረግ ይቻላል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል ።

የበሰቃ ሀይቅ ውሃ ወደ አዋሽ ወንዝ መለቀቁ በመካከለኛውና በታችኛው አዋሽ ተፋሰስ ነዋሪዎችና በልማቱ ላይ ተፅእኖ ይኖረው እንደሆን የአዋሽ ተፋሰስ ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ አቶ አበጀ መንገሻ ተጠይቀው በሰጡት መልስ ከሀይቁ እየተመጠነ ወደ አዋሽ የሚለቀቀው ውሃ የሚያስከትለው ጉዳት የለም ።

“አንዲያውም የሃይቁ ውሃ በየጊዜው ጥራቱ እየተሻሻለ በመምጣቱ ለመስኖ ልማት አገልግሎት የሚውልበት አማራጭ እየተፈለገ በመሆኑ ከአሁን በኋላ የበሰቃ ሀይቅ በረከት እንጂ ስጋት ሆኖ አይቀጥልም” ብለዋል ። 

በወረር ግብርና ምርምር ማእከል የዘርፉ ተመራማሪ አቶ አሸናፊ ወርቁ እንደገለፁት የበሰቃ ሀይቅ ውሃ የጥራት መጠኑ እያደገ መምጣቱንና በሒደት ለመስኖ ልማት መዋል እንደሚችል በጥናት መረጋገጡን አስረድተዋል ።

ከአዲስ አበባ እስከ ታችኛው አዋሽ አፍአምቦ ድረስ በዓመት 4 ጊዜ የአዋሽ ወንዝ የውሃ ጥራት ናሙና እንደሚወሰድ ገልፀው የበሰቃ ሀይቅም የውሃው የጥራት መጠን ከ7 ነጥብ 4 ዴሲ ሳይመን ወደ 3 ነጥብ 2 ዴሲ ሳይመን በመቀነስ መሻሻል እያሳየ መሆኑ ን ተናግረዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም