"ኩባ በሐረሪ ክልል በጤናው ዘርፍ የሚከናወኑ ሥራዎችን ለማጎልበት ትሰራለች''-አምባሳደር ቶማስ

60

ሐረር ግንቦት 6 /2011 የኩባ መንግሥት በሐረሪ ክልል በጤናው ዘርፍ የሚከናወኑ ሥራዎችን ለማጎልበት እንደሚሰራ በኢትዮጵያ የኩባ አምሳደር ተናገሩ።

አምባሳደር ቪልማ ቶማስ ከሐረሪ ክልላዊ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ዛሬ በተወያዩበት ወቅት እንደተናገሩት አገራቸው የክልሉን የጤና ዘርፍ እንቅስቃሴ ታግዛለች።

በዚህም በዘርፉ የሚካሄዱ የእውቀት ሽግግርና ልምድ ልውውጥ ለማጎልበት እገዛ ታደርጋለች ብለዋል።

አገራቸው በጤናና በትምህርት ዘርፎች ለኢትዮጵያ ድጋፍ እያደረገች መሆኗን ያስታወሱት አምባሳደሯ፣በተለይ ከክልሉ ጋር ባላት ታሪካዊ ግንኙነት በጤናው ዘርፍ ትብብሯን እንደምታሳድግ ተናግረዋል።

ከክልሉ መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በነበራቸው ውይይት የኩባና የክልሉ ሕዝብ ግንኙነትና ትብብር በሚጠናከርባቸው መስኮች ላይ መነጋገራቸውን አስታውቀዋል።

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወሂብ በድሪ በበኩላቸው ኩባ የክልሉን መንግሥት በጤናው ዘርፍ ልምድ እንዳላት አስታውሰው፣፤በአሁኑ ወቅትም አምስት የጤና ባለሙያዎች በዚያችው አገር ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ እንደ አብነት  አቅርበዋል።

በአምባሳደሯ ጉብኝት የእውቀት ሽግግርና የልምድ ተሞክሮዎችን ለማጠናከር ከስምምነት መደረሱንም  ገልጸዋል።

''ኩባውያን የኢትዮጵያ መንግሥትን በመደገፍ ውድ ህይወታቸውን ሰጥተዋል'' ኃላፊው፣ለዚህም በሐረር ከተማ የሚገኘው መካነ መቃብራቸው ህያው ምስክር ነው ብለዋል።

በአምባሳደር ቶማስ የተመራው ልዑካን ቡድን በክልሉ የሚገኙ ታሪካዊና ጥንታዊ መስህቦችና የኩባውያን መካነ መቃብር ጎብኝቷል።

ኢትዮጵያና ኩባ  ከ40 ዓመታት በላይ የዘለቀ ወዳጅነት አላቸው።

የአገሮቹ ግንኙነት የተጠናከረው በ1969 70 በኢትዮጵያ ሶማሊያ መካከል የተደረገውን ትብብር ተከትሎ ኩባ ወደ ኢትዮጵያ ወታደሮቿን ከላከች በኋላ መሆኑን ድርሳናት ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም