የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአውሮፓዊያኑ 2020 በተመሳሳይ ፍጥነት ያድጋል

110

አዲስ አበባ ግንቦት 6/2011   ኢትዮጵያና ኮትዲቩዋር ከእስያ ውጭ ካሉ አገራት እኤአ በ2020 ኢኮኖሚያቸው በተመሳሳይ ፍጥነት እንደሚያድግ አንድ ዓለም አቀፍ ሪፖርት አመለከተ::

በእንግሊዝ በሚገኘው ስታንዳርድ ቻርተርድ ባንክ እና ኤሲያን ማይክሮ ኢኮኖሚክ የምርምር ማዕከል የሚሰሩ የኢኮኖሚ ኤክስፐርቶች ባዘጋጁት ሪፖርት ከእስያ አገራት ውጭ ኢትዮጵያ እኤአ በ2020  ዘንድሮ ያስመዘገበችውን ተመሳሳይ የኢኮኖሚ እድገት ታሳያለች ብለዋል።

በእንግሊዙ ዘርፈ ብዙ ባንክ ስታንዳርድ ቻርተርድ የሚሰሩት ኢኮኖሚስቱ ክሪስቲያን ሮዝ እኤአ በ 2020 በእስያ ቀጠና የሚገኙ አገራት ኢኮኖሚ በ 7 በመቶ ያድጋል ብለዋል።

ባለፈው እሁድ ስታንዳርድ ቻርተርድ ያወጣው አዲስ ሪፖርት  እንደሚያሳየው ከእስያ ውጭ ካሉ የአፍሪካ አገራት የኢትዮጵያና ኮትዲቩዋር የኢኮኖሚ እድገት በነበረበት ፍጥነት ይቀጥላል ።

የተቀረው አለም የኢኮኖሚ እድገት ዘገምተኛ እንደሆነም ሪፖርቱ አመልክቷል።

በእስያና ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት የሚታየው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት አካባቢውን ለአመታት ቀፍድዶ የያዘውን ችግር ይቀርፋል ተብሎ ታምኖበታል።

ከፈጣን  እድገት የሚገኘው ከፍ ያለ ገቢ የማህበራዊ ፖለቲካ አለመረጋጋትን እንደሚቀንስ እሙን ነው።

በተጨማሪም አዳዲስ የመዋቅር ማሻሻያዎችን ለማከናወን ይረዳል”በማለት የስታንዳርድ ቻርተር ባንክ ኤከስፐርቶች በሪፖርታቸው አመላክተዋል።

“ፈጣን እድገት ብቻውን ብዙ ሰዎችን ከከፋ ድህነት ለማላቀቅ አያስችልም ፤ነገር ግን በተሻሻለ የጤናና የትምህርት አገልግሎት መታገዝ አለበት፤ በተጨማሪም የአገልግሎት አሰጣጡና የመሰረታዊ እቃዎች አቅርቦት የተሳለጠ መሆን አለበት”ብሏል ሪፖርቱ።

ያም ቢሆን ውስብስብ የሆኑ የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ማህበራዊ ጉዳዮችን በፍጥነት ማስወገድም ይገባል።

በርካታ የአስያና የአፍሪካ አገራት እድገታቸው ከፍተኛ ቢሆንም ሙስናን ለመዋጋት፣ ድህነትን ለመቀነስና ስራ አጥነትን ለማቃለል እየተጉ  ይገኛሉ።

ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ቁጠባንና ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት ህዝቦችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተገልጿል።

ባንኩ የኢኮኖሚ መለኪያዎችን በማውጣት ኢኮኖሚውን መመዝገብ ከጀመረበት ያለፉት አስር አመታት አንስቶ ኢትዮጵያ በተከታታይ ከ 7 በመቶ በላይ እድገት በማስመዝገብ ከቀዳሚዎቹ አስር አገራት አንዷ ሆና መቀመጧን ብሉምበርግ በዘገባው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም