በደቡብ ወሎ ዞን በ3 ሺህ ህፃናት ላይ በድብቅ ሊፈጸም የነበረ ያለእድሜ ጋብቻ ተቋረጠ

77

ደሴግንቦት 5 /2011 በደቡብ ወሎ ዞን በተያዘው ዓመት በ3 ሺህ ህፃናት ላይ በድብቅ ሊፈጸም የነበረ ያለእድሜ ጋብቻ መቋረጡን የዞኑ ሴቶችና ህፃናት መምሪያ አስታወቀ፡፡

በመምሪያ የሴቶች ንቅናቄና ግንዛቤ ማስፋፊያ ቡድን ባለሙያ አቶ ተፈሪ ሁሴን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በተደረገው የተቀናጀ ክትትል በዞኑ በድብቅ ሊዳሩ የነበሩ ህፃናትን ጋብቻ ማስቀረት ተችሏል፡፡

ጋብቻው የተቋረጠው ከኅብረተሰቡ የደረሰ ጥቆማን መነሻ በማድረግ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ነው።

ለጋብቻ እድሜያቸው ያልደረሰ ህፃናትን ጋብቻ በድብቅ  ፈፅመው የተገኙ የ91 ህጻናት ቤተሰቦች ለህግ ቀርበው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑን አስረድተዋል።

"ሙሽራው ወደ ሴቷ ቤት ሳይሄድ በድብቅ ቤተሰብ ሙሽራዋን ከሙሽራው ቤት አድርሶለት ይመጣል" ያሉት ባለሙያው፣ ይሄም ያለ እድሜ ጋብቻን ለመቆጣጠር አዳጋች አድርጎት እንደቆየ አብራርተዋል፡፡

በተለይ ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ሙስሊሙ ሰደቃ፣ ክርስቲያኑ ደግሞ በተስካርና  በሌሎች ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላት በማሳበብ ጋብቻ እንደሚፈጸም አስረድተዋል።

ከወንዱ ወይም ከሴቷ ቤተሰብ መሬትና ሀብት መፈለግና  ውለታና ጋብቻውን ለመደገስ የሚሰጡ ምክንያቶች መሆናቸውን አመልክተዋል።

በዞኑ የከላላ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ ይመር አስፋው በግንዛቤ እጥረት ምክንያት ለጋብቻ ያልደረሰች የ14 ዓመት ሴት ልጃቸውን ሊድሩ አስበው እንደነበር አስታውሰዋል።

"ሴት ልጅ ከ10 እስከ 20 ዓመት ባለው የእድሜ ክልል ውስጥ ካላገባች ቆሞ ቀር እየተባለች መተረቻ ከመሆኗም ባለፈ በባህሉ እንደ ነውር ይቆጠራል" ብለዋል።

በተፈጠረላቸው ግንዛቤ  የሴት ልጃቸውን ጋብቻ እንዲቋረጥ ማድረጋቸውን ያስታወሱት አቶ ይመር፣ ራሳቸውን ምሳሌ በማድረግ ስለ ያለእድሜ ጋብቻ አስከፊነት ለአካባቢው ነዋሪ እያስተማሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ ባለፉት ዓመታት በተከናወነ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ጠለፋ፣ የሴት ልጅ ግርዛት፣ ግግ ማስቧጠጥ፣ እንጥል ማስቆረጥን የመሰሉ  ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መቀነሳቸው ተገልጿል።

ባለፈው ዓመት የአንድ ሺህ 250 ህጻናት ያለዕድሜ ጋብቻ እንዲቋረጥ መደረጉን ከዞኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም