በየቀኑ በአማካይ ከ3 ሺህ የሚበልጡ ተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው እየተመለሱ ነው

80

ዲላ ግንቦት 3/2011 በየቀኑ በአማካይ ከ3 ሺህ የሚበልጡ ተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው በመመለስ ላይ መሆናቸውን የጌዴኦ ዞን አደጋ ስጋትና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

በአራት ቀናት ውስጥም ከ15 ሺህ የሚበልጡ ተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው ተመልሰዋል፡፡

የጌዴኦ ዞን አደጋ ስጋትና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ትዕግስቱ ገዛኸኝ በምዕራብ ጉጂ ዞን ያለው የጸጥታ ሁኔታ እየተሻሻለ በመምጣቱ የተመላሽ ተፈናቃዮች ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዞኑ በተለይም በገደብ ወረዳ 13 መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የነበሩ ተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡

ባለፉት አራት ቀናት ውስጥም ከ15 ሺ 200 በላይ ዜጎች ከጌዴኦ ዞን ወደ ምዕራብ ጉጂ ዞን መሄዳቸውን አስረድተዋል፡፡

ተመላሽ ተፈናቃዮች በቄያቸው ያጋጠማቸው አቀባበል መልካም መሆንና በምዕራብ ጉጂ ዞን በተለይም በቀርጫ ወረዳ ካለው አንጻራዊ ሰላም ጋር ተዳምሮ የተመላሾችን ቁጥር አሳድጎታል ብለዋል፡፡

በጊዜያዊ መጠሊያ ጣቢያዎች የሚገኙትን ተፈናቃዮች በአጭር ጊዜ  ውስጥ ወደ ቄያቸው ለመመለስ የዞኖቹ አመራሮችና የጸጥታ አካላት ተቀናጅተው በመስራት ላይ መሆናቸውን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ከጌዴኦ ዞን ወደ ምዕራብ ጉጂ ዞን ከሄዱ ዜጎች ውጭም ከ6ሺህ የሚበልጡ ተፈናቃዮች ወደ አካባቢያቸው መመለሳቸውን አመልክተዋል፡፡

የምዕራብ ጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበራ ቡኖ በበኩላቸው ተፈናቃዮቹ ከዞኑ ማዕከል እንዲሁም ከጌዴኦ ዞን ወደ ቄያቸውን ዜጎች እየተመለሱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ከሚመልሳቸው ዜጎች ውጭ በርካታ ተፈናቃዮች በራሳቸው ተነሳሽነት ወደ ቄያቸው በመመለስ ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

ተፈናቃዮቹ ወደ ቄያቸው ሲመለሱም ችግር እንዳይገጥማቸው ኅብረተሰቡን በተለይ መጠለያ ቤቶችን በመሥራት አንስቶ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከተመላሽ ተፈናቃዮች መካከል አቶ አሰፋ ዶሪ በሰጡት አስተያየት ላላፉት 13 ወራት በጌዴኦ ዞን መጠለያ ጣቢያ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በምዕራብ ጉጂ ዞን ቀርጫ ወረዳ 02 ቀበሌ በሚገኘው ቤታቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡

ቄያቸው ሲደርሱ በተደረገላቸው አቀባበል መደሰታቸውን ገልጸው፣ መንግሥት የወደመውን ሃብት ንብረታቸውን ለመተካት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡

በጌዴኦ ዞን ከ900ሺህ በላይ ተፈናቃዮች እንደነበሩ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም