የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሠላም ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚደረገው እንቅስቃሴ ይጠናከራል---ኮማንድ ፖስቱ

97

ሚዛን ግንቦት 2 / 2011  የአካባቢዎቹን ሠላም ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንደሚያጠናክር የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት አስታወቀ።

በካፋ፣ ሸካ ፣ቤንች ሸኮና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች  መጋቢት 21/2011 ጀምሮ ባከናወናቸው ተግባራት ላይ መግለጫ  ሰጥቷል።

የዞኖቹ ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ኮሎኔል ተስፋዬ ሊላይ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ኮማንድ ፖስቱ በአካባቢዎቹ በተከሰተው የጸጥታ ችግር የተጓደለውን ሰላምና ደህንነት ወደ ነበረበት ለመመለስ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

በዞኖቹ  ወደ መኖሪያቸው ያልተመለሱ ተፈናቃዮችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ለመመለስ  እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

በግጭቱ ምክንያት የተዘጉ መንገዶች ተከፍተው አገልግሎት መጀመራቸውን አመልክተዋል፡፡

በግጭቱ የተሳተፉና የተጠረጠሩ ከ1ሺህ 100 በላይ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸው እየታየ ይገኛል ብለዋል፡፡

በግጭቱ ምክንያት ከተፈናቀሉት ከ34 ሺህ በላይ ዜጎች መካከል ከ9ሺህ የሚበልጡትን ዜጎች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡

ከግለሰቦች፤ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት የተዘረፉ 145 ሽጉጦች፣ የእጅ ቦምቦችና ዘመናዊና ኋላ ቀር የጦር መሣሪያዎች ማስመለሱንም ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በፍተሻ ጣቢያዎች በተደረገ ቁጥጥርና ፍተሻ 71 የጦር መሣሪያዎችን መያዛቸውን ኮሎኔል ተስፋዬ አስታውቀዋል፡፡

ኮማንድ ፖስቱ  ለተጨማሪ 15 ቀናት መራዘሙን ያስታወቁት አስተባባሪው፣በዚህም ጊዜ የአካባቢዎቹን ሠላም ወደ ነበረበት ሁኔታ ለመመለስ ጥረቱን ያጠናክራል ብለዋል፡፡

በአካባቢዎቹ ባለፉት ዓመታት በተፈጠሩ ግጭቶች ሰላማዊ ሕይወት ከመስተጓጎሉም በላይ፤ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ችግር ውስጥ ወድቆ እንደነበር ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም