ጋሕነን በክልሉ ሰላማዊ ትግል በማካሄድ ለሰላምና ልማት መስፈን ድርሻውን ይወጣል

ጋምቤላ ግንቦት 2 /2011 በክልሉ ሰላማዊ ትግል በማካሄድ ሰላምና ለልማት መስፈን ድርሻውን እንደሚወጣ የጋምቤላ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ/ጋሕነን/ አስታወቀ፡፡

በቅርቡ ከኤርትራ ወደ ክልሉ የገቡት የንቅናቄው አመራሮችና አባላት ለሁለት ሳምንታት የተሰጠው የተሃድሶ ስልጠና ተጠናቋል፡፡

የንቅናቄው ሊቀመንበር አቶ ኡኬሎ ኡኪዲ በዘዚሀ ወቅት እንደገለጹት ድርጅቱ በክልሉ ሰላማዊ ትግል በመሳተፍ  የህዝቡን ሰላም፣ልማትና መልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ድርሻውን ይወጣል፡፡

እንደ አገር የተጀመረው የፖለቲካ ምህዳር መስፋት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ህዝቡ ገብተው ሰላማዊ ትግል እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታን መፍጠሩን አመልከተው፣በዚህም ንቅናቄው በክልሉ ፖለቲካዊ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ሚና ለመወጣት ያስችለዋል ብለዋል፡፡

ስልጠናው ወደፊት ከህዝቡ ጋር በመቀላቀል ለክልሉ ሰላም፣ልማትና መልካም አስተዳደር ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት እንደሚረዳም ሊቀመንበሩ ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ እንዳሉት መንግሥት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ አገር ውስጥ በመግባት ሰላማዊ ትግል እንዲያደርጉ የፈጠረው ምቹ ሁኔታ ተጠቅሞ ወደ ክልሉ የገባው ጋሕነን ለክልሉ ህዝብ ተጠቃሚነት እንዲሰራ አሳስበዋል፡፡

የክልሉ መንግሥትም ከተፎካካሪ ፓርቲዎች  ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ድርጅቱ ሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ አገር ውስጥ  የገባው ባለፈው ወር ነበር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም