በኦሮሚያ ክልል የተካሄደው ውይይቱ ግጭት እንዲፈጠር የሚያደርጉ አካላትን ለማጋለጥ ህዝቡ አቋም የያዘበት ነው-- ኦዴፓ

84

ግንቦት 2/2011 በኦሮሚያ ክልል ባለፉት አራት ቀናት የተካሄደው ህዝባዊ መድርክ ህዝቡ ግጭት የሚፈጥሩ አካላትን ለማጋለጥ አቋም የያዘበት መሆኑን የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) አስታወቀ።

የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ አካላትን ለማጋለጥ አቋም መያዛቸውን ኦዴፓ አስታወቀ።


የክልሉ መንግስት ላለፉት አራት ቀናት በየደረጃው ካሉ የክልሉ ነዋሪዎች ጋር አብሮነትንና ሰላምን መሰረት ያደረገ ህዝባዊ ውይይት አካሂዷል።

የኦዴፓ መዕከላዊ ፅህፈት ቤት የህዝብ አስተያየትና የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ታዬ ደንደአ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ህዝባዊ ውይይቱ የተሳካና ህዝቡ በግጭት ቀስቃሽነት የሚሳተፉ አካላትን አጋልጦ ለመስጠት አቋም ወስዷል።

ውይይቱ በክልሉ የሚኖሩ ህዝቦችን አንድነትና አብሮነት በማጠናከር የክልሉን ሰላም አስትማማኝ ማድርግ ያለመ ሲሆን ህዝቡም ይህንኑ አቋሙን ያረጋገጠበት አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በማህበራዊ ሚዲያና በአንዳንድ መደበኛ መገናኛ ብዙሃን ጭምር ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የሚሰሩ በመኖራቸው የእስካሁኑ የግጭት መንስኤም ይሄው መሆኑን ጠቁመዋል።

ግጭት ቀስቃሽ መረጃዎችን የሚለቁ የመገናኛ ብዙሃንን መንግስት ተከታትሎ እርምጃ መውሰድ እንዳለበትም በመድረኩ ላይ ከህዝቡ ጥያቄ ተነስቷል ብለዋል።

በግለሰብም ይሁን በድርጅት ከግጭት ትርፍ ለማግኘት በማሰብ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ አካላትን በማጋለጥ ከፀጥታ ሃይሉ ጋር እንሰራለን ሲሉም የመድረኩ ተሳታፊዎች አቋም መያዛቸውን አቶ ታዬ ገልፀዋል።

የክልሉ ምንግስት የህዝቡን ሰላም ለማስጠበቅና የህዝቦች አብሮነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከምንጊዜውም በላይ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።

ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት በማሰብ መረጃ የሚያሰራጩ ግለሰቦች፣ ድርጅቶችና የመገናኛ ብዙሃንም ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም