በአቶ ጌታቸው አሰፋ የክስ መዝገብ ስር ያሉ ተከሳሾች የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጡ

554

አዲስ አበባ ግንቦት 1/2011 በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የወንጀል ችሎት የዛሬ ውሎ በጌታቸው አሰፋ የክስ መዝገብ ውስጥ ካሉ 26 ተከሳሾች መካከል ሃያ አንዱ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ከትናንት በስቲያ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል በሚል ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ በ26 የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ላይ ክስ መመስረቱ የሚታወስ ነው።

አቃቤ ህግ በ26ቱ ተከሳሾች ላይ 46 ክሶችን የመሰረተ ሲሆን ክሶቹ ከትናንት በስቲያ ጀምሮ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የወንጀል ችሎት ሲነበብ ቆይቷል።

 በዛሬው የችሎቱ ውሎም ትናንት ከቆመበት ከ35ኛ እስከ 46ኛ ያሉ ክሶች በችሎቱ በንባብ የተሰማ ሲሆን በአጠቃላይ በቀረቡት ክሶች 131 የሰው እና 12 ልዩ ልዩ የሰነድ ማስረጃዎች እንደቀረቡም በክስ መዝገቡ ላይ ተገልጿል።

ችሎቱ በክስ መዝገቡ ካልተያዙት 1ኛ ተከሳሽ ጌታቸው አሰፋ፣ 9ኛ ተከሳሽ አፅብሃ ግደይ፣ 11ኛ ተከሳሽ  አሰፋ በላይ እና 12 ተከሳሽ ሺሻይ ልዑል በስተቀር ለሁሉም የተነበበው የክስ ይዘት ግልጽ ነው አይደለም የሚለውን ጥያቄ አቅርበው በችሎቱ የተገኙት 22 ተከሳሾች ክሱ ግልጽ እንደሆነ ለችሎቱ ተናግረዋል።

ችሎቱ ለተከሳሽ ጠበቆች የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ካላቸው እንዲያቀርቡ ጠይቆ ከ21ኛ ተከሳሽ ሰይፈ በላይ በስተቀር ሌሎቹ ተከሳሾች ምንም አይነት የክስ መቃወሚያ እንደሌላቸውና የፍርድ ሂደቱ ምስክር ወደ መስማት እንዲሄድ በጠበቆቻቸው በኩል ለችሎቱ አሳውቀዋል።

21ኛ ተከሳሽ አቶ ሰይፈ በላይ ከጠበቃው ጋር ተማክሮ በቀጣይ ቀጠሮ የክስ መቃወሚያ እንደሚያቀርብ ለችሎቱ ገልጿል።

በመቀጠልም ችሎቱ የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል የተቀበለ ሲሆን ከ21ኛ ተከሳሽ አቶ ሰይፈ በላይ በስተቀር ቀሪ 21 ተከሳሾች የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

21ዱም ተከሳሾች ለችሎቱ የተባለውን የወንጀል ድርጊት አልፈጸምንም ጥፋተኛ አይደለንም የሚል የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

21ኛ ተሳከሽ ሰይፈ በላይ የክስ መቃወሚያ አለኝ በማለቱ በህጉ መሰረት የእምነት ክህደት ቃል መስጠት እንደማይችል ችሎቱ አስረድቷል።

የዋስትና መብትን በተመለከተ ችሎቱ የተከሳሽ ጠበቆች የሚያቀርቡት አቤቱታ ካለ እንዲያቀርቡ ጠይቆ ጠበቆች አቤቱታቸውን አቅርበዋል።

አንድ ተከሳሽ ወይም ተጠርጣሪ ዋስትና የማግኘት መብት ህገ መንግስታዊ እንደሆነና የዋስትና መብቱም በልዩ ሁኔታዎች እንደሚከለከሉ እና በአጠቃላይ ተከሳሾች የተከሰሱበት ወንጀል የዋስትና መብታቸውን የሚያስነፍግ እንዳልሆነ የተከሳሽ ጠበቆች ተናግረዋል።

የቀረቡት ክሶች ተደምረው ተከሳሾቹ ጥፋተኛ ቢባሉ እንኳን ከ10 ዓመት በታች የሚያስቀጣ በመሆኑ በህጉ መሰረት ከ10 ዓመት በታች ለሚያስቀጣ ወንጀል የዋስ መብት የሚከለከል ባለመሆኑ ተከሳሾች የዋስትና መብታቸው ተከብሮ በውጭ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ጠይቀዋል።

አቃቤ ህግ በበኩሉ ከጠበቆች በኩል ያሉትን የህግ ድንጋጌን በተመለከተ የተነሱ ሀሳቦች በዋስትና መብት ክርክር ሳይሆን በክስ መቃወሚያ ላይ የሚቀርቡ መሆናቸውን የገለጸ ሲሆን ከ21ኛ ተከሳሽ በስተቀር ሌሎቹ የክስ መቃወሚያ የለንም ማለታቸውን ለችሎቱ ገልጸዋል።

የድንጋጌው ጉዳይ በአጠቃላይ የዋስትና መብት የሚያስከለክለው ከ7 እስከ 15 ዓመት በሚያስቀጡ ወንጀሎች እንደሆነ በመግለጽ የተከሳሽ ጠበቆች ያቀረቡትን የዋስትና መብት ጥያቄ ተቃውሟል።

ተከሳሾቹ ካላቸው የስራ ሃላፊነት አንጻር ቢወጡ እነሱን መልሶ ችሎት ማቅርብ እንደማይቻልና በዋስትና ቢወጡ ማስረጃዎችን ስለሚያጠፉ ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብት ጥያቄውን ውድቅ እንዲያደርገው አቃቤ ህግ ችሎቱን ጠይቋል።

በተጨማሪም ችሎቱ የምስክሮችን ቃል ወደ መስማት እንዲሸጋገርም አቃቤ ህግ ጠይቋል።

የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው በአሁኑ ሰአት ተካሳሾቹ ወደ ቀድሞው የስራ ድርሻቸው መመለስ እንደማይችሉና አብዛኞቹ ተከሳሾች ተራ ሰራተኞች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ማስረጃ ማጥፋትን በተመለከተ አቃቤ ህግ ድምጽ እየቀረጸ ለሁለት ወራት ተካሳሾች በሌሉበት በቀዳሚ ምርመራ የምስክር ቃሎችን መቀበሉንና ተካሳኞችም ምስክሮችን እንደማያውቁና የሰነድ ማስረጃዎችም አቃቤ ህግ ጋር እንደሚገኙ በመግለጽ ተካሳሾች ምንም ሊያጠፉት የሚችሉት የሰነድ ማስረጃ እንደሌለ ገልጸዋል።

20ኛ ተከሳሽ አቶ እዮብ ተወልደ ለችሎቱ አቤቱታ አለኝ ብለው ባቀረቡት ” ከተያዝን ስድስት ወር ሆኖናል፤ ስንያዝ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ስብሰባ አለ ተብለን በሰርቪስ ስንሄድ ፌደራል ፖሊሶች ያለንን አጠቃላይ ንብረት ወስደው ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ነው የተያዝነው” ብለዋል።

ቀዳሚ ምርመራ የምስክር ቃል አቃቤ ህግ ከተቀበለ በኋላ ለሁለት ወር ከ8 ቀን ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ እስር ቤት ቆይተናል፣ የአካል ደህንነት መብታችን ይከበር ብለን ፍርድ ቤት ጠይቀን ቀጠሮ በሰጠን ቀን ነው ፖሊሶች ፌደራል ፍርድ ቤት ትሄዳላችሁ ብለው ፍርድ ቤት የመጣነው፣ ፍርድ ቤት ቀጠሮ እንዳለብን አቃቤ ህግ አውቆ ነው የዛኑ ቀን ክሱን የመሰረተው ብለዋል።

በተለያዩ ሁኔታ ከባድ የሰብዓዊ መብት የፈጸሙ ሰዎች ጊዜው የይቅርታ ጊዜ ነው ተብሎ ምህረት ተደርጎላቸው ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖሩ እኛ ላለፉት 20 ዓመታት ከቤተሰብ ተለይተን አገር በታማኝነት ያገለግልን ሰዎች ላይ እንዲህ አይነት እንግልት መድረሱ ተገቢነት የለውም ብለዋል።

የተከሳሾች የባንክ አካውንት ተዘግቷል፤ ደመወዝ ለአምስት ወር አልተከፈለንም የተከሳሽ ቤተሰቦች ከቤታችሁ ውጡ በሚል ጫናና ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው ነው፤ ገቢ ባለማግኘታችን ምክንያት ልጆቻችን በጥሩ ሁኔታ ላይ አይገኙም፤ ከዚህ በላይ የሰብዓዊ  መብት ጥሰት የለም ሲሉም አቶ እዮብ ገልጸው ፍርድ ቤቱ ለተከሳሾች ፍትህ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

ችሎቱ ተከሳሾች ጠበቆቻቸውን አማክረው ያላቸውን ቅሬታ በጽሁፍ እንዲያቀርቡ እና የጥያቄውንም ተገቢነት አይቶ ውሳኔ እንደሚያስተላልፍ ገልጿል።

ጠቅላይ አቃቤ ህግ በትናንት የችሎት ውሎው ያልተያዙት 1ኛ ተከሳሽ ጌታቸው አሰፋ 9ኛ ተከሳሽ አፅብሃ ግደይ 11 ተከሳሽ  አሰፋ በላይ እና 12 ተካሳሽ ሺሻይ ልዑል በፌደራል ፖሊስ በኩል መጥሪያ እንዲሰጣቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቆ ነበር።

ችሎቱ ዛሬ በሰጠው ውሳኔ መሰረት የፌደራል ፖሊስ ያልተያዙ ተከሳሾች ያሉበትን ቦታ አፈላልጎ መጥሪያ እንዲያደርሳቸው ትዕዛዝ ሰጥቷል።

የፌደራል ፖሊስ መጥሪያውን አስመልክቶ ያለበትን ደረጃ እንዲያቀርብ፣21ኛ ተከሳሽ ሰይፈ በላይ የክስ መቃወሚያ ካላቸው መቃወሚ እንዲያቀርቡ ከሌላቸው የእምነት ክህደት ቃል እንዲሰጡና በዋስትና መብት ክርክሩ ላይ ብይን ለመስጠት ችሎቱ ለግንቦት 8 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።