የኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ በሳይንሳዊ ዕውቀት ባለመደገፉ ለአገሪቷ ምግብ እጥረትና ወጪ ምርት መጓደል ምክንያት ሆኗል- ጥናት

123

አዲስ አበባ ግንቦት 1/2011 ኢትዮጵያ በሳይንሳዊ እውቀት የተደገፈ የግብርና ልማት ባለማካሄዷ ከወጪ ምርት አቅርቦት መጓደል ባሻገር ራስን መመገብ የሚያስችል ምርት ማምረት እንዳዳገታት ጥናቶች አመለከቱ።

የአገሪቷ የጀርባ አጥንት የሆነውና 90 በመቶ የወጪ ምርትን የሚሸፍነው ግብርና ከቆየው የዘልማድ አሰራር ካልወጣ አገሪቱ  ከዘርፉ የምትጠብቀውን ግብ ማሳካት እንደማይቻል ጥናቶቹ አመላክተዋል።

ዛሬ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት በተካሄደው ውይይት ላይበዘጠኝ ዋና ዋና የግብርናው ዘርፍ ችግሮችን በመጠቆም ዘመናዊ አሰራር መፍጠር የሚቻልባቸው መፍትሄዎች አመላክተዋል።

ጥናቶቹን ያካሄዱት ከዩኒቨርሲቲዎችና ግብርና ምርምሮች የተውጣጡ 54 የመስኩ ምሁራን ሲሆኑ ጥናቶቹም አገሪቷ እስካሁን በሚታቀደውና በተነገረው ልክ በግብርናው ለምን ውጤታማ አልሆነችም ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ነው።

ጥናቶቹየግብርና ግብዓት አቅርቦት እጥረት፣ በመስኩ ያለው ተቋማዊ የአመራር ሁኔታ፣ የግብርና ሜካናይዜሽን ያለበት ችግር፣ የመስኖ አጠቃቀምና ችግሮቹ፣ የተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤና አጠቃቀምን ዳሷል። 

በመስኩ ስለሚካሄዱ የጥናትና ምርምር ተግባራት፣ አጠቃላይ የግብርና ኤክስቴንሽን አተገባበር፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የግብርና ኮሜርሻላይዜሽንም እንዲሁ ጥናቶቹ ትኩረት ያደረጉባቸው መስኮች ናቸው።

ጥናታቸውን ካቀረቡት መካከል የኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈቶ እስሞ እንደገለጹት፤ ከተለመደው የግብርና አሰራራችን ካልወጣን አምርተን ወደ ውጭ መላክ ቀርቶ በምግብ ራሳችንን መቻል አዳጋች ነው።

ዶክተር ፈቶ አክለውም "ግብርናችንን እስካሁን አንቆ የያዙ ችግሮችን በሳይንሳዊ እውቀት ለይተን መፍትሔ ማስቀመጥ አለመቻላችን በመሆኑ ከዚህ የሚያላቅቅ ጥናት ሊኖረን ይገባል" ብለዋል።

በዘር ልማትና አቅርቦት ላይ ያተኮረ ጥናት ያቀረቡት እና በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ታዬ ተሰማ በበኩላቸው ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አስተሳሰብን መለወጥ እንደሚገባን ጠቁመዋል።

"የእርሻን ክቡርነት ከማዕዱ በፊት ባለው  የእርሻ ተግባራት ጭምር ጭቃ ውስጥ ገብቶ መስራትን ይጠይቃል" ያሉት ዶክተር ታዬ ለግብርና ያለን አተያይ አምራቹ ገበሬን ከማክበር እንደሚጀምርም ተናግረዋል።

ከጥናት ቡድኖቹ  አስተባባሪና በሴክተሩ በአመራርነትና በባለሙያነት ሰፊ ልምድ ያላቸው ዶክተር አበራ ዴሬሳም በሳይንስ እውቀት ያልተመራ ግብርና የታለመለትን ግብ ማሳካት እንደማይችል ነው የሚናገሩት።

ተነሳሽነቱን ወስዶ አገሬን ልርዳ ለሚለው ምሁራን ቁጭ ብሎ የሚሰማ መሪ እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ዶክተር አበራ በዛሬው ውይይት ቁጭ ብሎ ሰምተው አቅጣጫ የሰጡትን የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳና የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴንን አድንቀዋል።

የቀረቡት ጥናቶች በውይይት ከዳበሩ በኋላ አጠቃላይ አቅጣጫ ያስቀመጡት የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር በበኩላቸው ሰው መማሩ ልዩ የሚያደርገው ከደሞዙ ባሻገር ለወገን የሚተርፍ ስራ ሰርቶ ማለፉ ነው ብለዋል።

"እስካሁን እንደ አገር የቸገረንም ምሁራን ተገፍተውና ከዳር ቆመው ከማየትና አስተያየታቸውን በሩቁ ከመሰንዘር አልፈው ወደ ተጨባጭ ስራ አለመግባታቸው" ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ግብርና በመስኩምሁራን እንዲመራና ምሁራኑም የራሳቸውን አሻራ አስቀምጠው እንዲያልፉ  በመንግስት አቅጣጫ  መያዙንም ገልፀዋል።

የኦሮሚያ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው አጠቃላይ የአገሪቱ ምጣኔ ኃብት ዋናው መሰረት የሆነው ግብርና በተለየ እውቀት መመራት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።

"እስካሁን ባለው ሁኔታ ግብርና ትኩረት አግኝቷል የሚባለው ሐሰት" መሆኑን ያወሱት አቶ ሽመልስ፡ "በወረቀትና በንግግር ብቻ ትኩረት የተሰጠውን የግብርናው ዘርፍ በመለወጥ ዜጎችን ከችግር ማላቀቅ አለብን" ብለዋል።

ይህንን ለማድረግም በራሳቸው ተነሳሽነት የሴክተሩን ችግሮች ለይተው በጥናት ያመጡትን ምሁራን አመስግነው የጥናቶቹን ውጤቶች ወደ ተግባር ለመለወጥ መንግስታቸው ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል ምክትል ፕሬዝዳንቱ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም