የአትክልትና ፍራፍሬ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ትኩረት ይፈልጋል—የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች

283

የአትክልትና ፍራፍሬ ዋጋ በአሳሳቢ ሁኔታ እየጨመረ በመሆኑ በኑሯቸው ላይ ጫና መፍጠሩን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

የዋጋ ጭማሪው እየታየ ያለው በወቅታዊ ሃገራዊ የገበያ መለዋወጥ ምክንያት መሆኑን የክልሉ ንግድ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ አስታውቋል።

ወጣት አክበረት ሚኪኤለ እንዳለችው፣በከተማው በአትክልትና ፍራፍሬ ላይ በየጊዜው የሚስተዋለው የዋጋ ጭማሪ ምክንያቱ ግልጽ አይደለም።

“ቀደም ሲል የተሻለ ጥራት ያለው ፍራፍሬ በጥሩ ዋጋ እንገዛ ነበር” ያለችው ወጣቷ፣ “በተለይ በሙዝና ብርቱካን ምርቶች የዋጋ መጨመር ብቻ ሳይሆን የጥራትና የጣዕም ችግርም ይታያል” ብላለች።

አንድ ኪሎ ሙዝ በ18 ብር ስትገዛ እንደነበረችና ዛሬ ላይ ኪሎውን በ25 ብር እንዲሁም እስከ 35 ብር ይሸጥ የነበረው አንድ ኪሎ ብርቱካን እንደ ጥራት ደረጃው ከ60 እስከ 80 ብር እየተሸጠ ይገኛል።

በመቀሌ ከተማ የሄለና ሱፐር ማርኬት ባለቤት ወይዘሮ ሳምራዊት ክንዳያ በበኩላቸው፣“ከሌሎች ክልሎች ይገቡ የነበሩ የሙዝና ብርቱካን ምርቶች በመቀነሳቸው ምክንያት ዋጋቸውን በየጊዜው እንድንጨምር ተገደናል” ብለዋል።

“ቀደም ሲል 15 ብር ይሸጥ የነበረ አንድ ኪሎ ሙዝ አሁን ላይ በ25 ብር ፣35 ብር ይሸጥ የነበረ አንድ ኪሎ ብርቱካን ደግሞ 60 ብር እና ከዚያ በላይ በመሸጥ ላይ እንገኛለን” ሲሉ ተናግረዋል።

“በተለይ ከአርባምንጭ ይመጣ የነበረ የሙዝ ምርት በአገሪቱ ውስጥ በተፈጠረው የሰላም ችግር ምክንያት ወደ ከተማው ስለማይመጣ ምርቱ የለም” ብለዋል።

ቀደም ሲል የአንድ ተሽከርካሪ ለጭነት ሲከፈል የነበረው ሰባት ሺህ ብር ዋጋም ወደ 10 ሺህ ብር በማሻቀቡ ለምርቶቹ መጨመር ምክንያት እነደሆነ ተናግረዋል።

ወጣት መስፍን ጌቱ ባለፈው አመት ከአዲስ አበባና ከሌሎች የአገራችን አከባቢዎች አትክልትና ፍራፍሬ በማስመጣትና በመቀሌ ከተማ በማከፋፈል ስራ ተሰማርቶ እንደነበር ያስታውሳል።

ቢሆንም በአገሪቱ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር መንግዶች በመዘጋጋታቸው ምክንያት ከ150 ሺህ ብር በላይ የገዛው ፍራፍሬ ከጥቅም ውጪ እንደሆነበት እና ስራውን ሙሉ በሙሉ ማቆሙን ተናግረዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከትግራይ ደቡባዊ ዞን ከራያ ዓዘቦ ወረዳ የተለያዩ የፍራፍሬ አይነቶችን ወደ መቀሌ በማምጣት መሰማራቱን የገለጸው ወጣቱ ፤ አሁን ያለው ፍራፍሬ በቂ ባይሆንም ወረዳው ከተሰራበት የተሻለ ምርት ሊገኝበት የሚችል መሆኑን ገልጿል።

የትግራይ ክልል ንግድ፣ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ዳኒኤል መኮንን በበኩላቸው፣በሃገር አቀፍ ደረጃ ያጋጠመው የዶላር እጥረት በሁሉም ምርቶችና ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዲከሰት አድርጓል።

በዚህም ምክንያት ፍራፍሬ አምራች አርሶ አደሮችም ሌላ የሸቀጣ ሸቀጦችንና ምርቶችን ለመግዛት የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ስለሚያጋጥማቸው በምርቶቻቸው ላይ ዋጋ እንዲጨምሩ ስላስገደዳቸው መሆኑን ተናግረዋል።

“በሌላ በኩል በአገሪቱ ባለው የፀጥታ ችግር ከተለያየ ቦታ በብዛት ይመጣ የነበረው የፍራፍሬ ምርት መቀነሱም ሌላው የዋጋ ጭማሪ ምክንያት ነው” ብለዋል።

“ሆኖም የሙዝ ምርትን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የክልላችን አቅም መጠቀም መጀመሩን እንደ ጥሩ ተሞክሮ መወሰድ አለበት” ብለዋል።

ሁሉም ህብረተሰብ ሸማች በመሆኑ በሚይዘው ምርት ላይ ዋጋ ከመጨመር ይልቅ በክልሉ የተረጋጋ ገበያ እንዲኖር የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አሳስበዋል።