በሆሳዕና ከተማ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከል ሞተረኞች ትብብር እንዲያደርጉ ተጠየቀ

57


ሆሳዕና ግንቦት 1 / 2011 በሆሳዕና ከተማ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከል የሞተር አሽከርካሪዎች ከፖሊስ ጋር በቅንጅት እንዲሰሩ ተጠየቀ፡፡

የከተማው ፖሊስ ጽህፈት ቤት የትራፊክ አደጋ መከላከልና ቁጥጥር ዋና የሥራ ሂደት ባለቤት ኮማንደር ዓለማየሁ ባቾሬ ፖሊስ ከከተማ ሞተረኞች ጋር  ዛሬ  ሲወያዩ  እንደተናገሩት የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ትብብራቸውን ጠይቀዋል፡፡

''ጨለማን ተገን በማድረግ በአንዳንድ ሞተረኞችና ግለሰቦች የሚፈጸሙ ወንጀሎች መበራከታቸውን ጥቆማዎች ያመለክታሉ'' ያሉት  ኮማንደር ዓለማየሁ፤ፖሊስ በመረጃ ላይ ተመስርቶ እርምጃ እንዲወስድ ትብብር ያስፈልገዋል ብለዋል።

ሞተረኞችን ጨምሮ ከኅብረተሰቡ ጋር በቅንጅት በመስራት ውጤታማ ለመሆን  እንደሚያስችለውም ገልጸዋል፡፡

የኅብረተሰቡ አካል የሆኑት የከተማው ሞተረኞች ለችግሩ ተጋላጭና ለመፍትሄው አስተዋጽኦ ያላቸው በመሆኑም ወንጀልን በመከላከል ድርሻቸውን እንዲወጡ ታስቦ ውይይቱ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ ከተሳተፉት ሞተረኞች መካከል አንዱ የቤተሰብ አስተዳዳሪ በመሆኑ ሥራውን እስከ ሌሊቱ ስድስት ሰዓት ስለሚሰራ ችግሩን እንደሚመለከት ገልጿል።

ከሞተረኞች መካከል ለሥራ የሚወጡ አስመስለው ዝርፊያ የሚፈጽሙ ሞተረኞችም እንዳሉ አመልክቷል፡፡

በተለይም በከተማው ከምሽቱ ሦስት ሰዓት በኋላ የሚወጡ አንዳንድ ሞተረኞችና ሠሌዳ የሌላቸው ሞተር ቢስክሌቶች መበራከት ለችግሩ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ብሏል፡፡

እነዚህን አካላት በመጠቆም ከፖሊስ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም አስታውቋል፡፡

ሌሊት ለሥራ በሚንቀሳቀስበት ወቅት ጨለማን ተገን በማድረግ ዝርፊያና ጥቃት የሚያደርሱ ግለሰቦችን እንደሚመለከት የተናገረው ደግሞ ሌላ ሞተረኛ  ነው፡፡

በነዋሪዎች ላይ በሽምቅ አደጋ የሚደርስባቸው ቦታዎች እንዳሉ የጠቆመው ይኸው አስተያየት ሰጪ፤ ወንጀልን ለመከላከል ከፖሊስ ጋር ተቀናጅቶ  ለመስራት ፈቃደኛ መሆኑን አስታዉቋል፡፡

በውይይቱ ላይ ከ400 በላይ ሞተረኞች ተሳትፈዋል፡፡

ሆሳዕና በደቡብ ብሄሮች፣ በህረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የሐዲያ ዞን ርዕሰ ከተማ ስትሆን፤ከ80ሺህ በላይ ነዋሪዎች እንዳሏት ይገመታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም