የኢትዮጵያ የአጋርነት ጉባኤ በዋሽንግተን ዲሲ ሊዘጋጅ ነው

58

ግንቦት 1/2011 የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ የአጋርነት ጉባኤ በዋሽንግተን ዲሲ ሊያዘጋጅ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የአሜሪካና ኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ትብብር አስመልክቶ የሚዘጋጀው ጉባኤ ኢትዮጵያ እያከናወነችው ያለውን አዲስ የኢኮኖሚ ሽግግርና የንግድ አማራጭ አመቺነት ሂደትን ለማሳየት ያለመ ነው።

የውይይት መድረኩ ግንቦት 7 እና 8 2011 ዓ.ም. በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢሮ  በሎይ ሄንደርሰን አዳራሽ እንደሚከናወን ተገልጿል።

ሁለቱ አገሮች የሚሳተፉበት ዝግጅት በኢትዮጵያ ያለውን የአሜሪካንን ኢንቨስትመንትና ተሳትፎ ከማሳደግ ባለፈ የኢትዮጵያን ንግድና ኢኮኖሚ ወደ አንድ ምዕራፍ ለማሳደግ ያለመ ነው።

በጉባኤው የመጀመሪያ ቀን ውሎ የፓናል ውይይት፣ ቁልፍ መልዕክቶች፣ የትብብር ምክክርና የመንግስት እና የግሉ ዘርፍ የንግድ አማራጮችን የተመለከቱ ጉዳዮች ይዳሰሱበታል ተብሏል።

በሁለተኛው ቀን ደግሞ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተዘጋጁና የኢትዮጵያ አጋርነት ጉባኤን የተመለከቱ ጥልቅ ጉዳዮች ይዳሰሱበታል።

ኢትዮጵያ እድገቷን ለማስቀጠልና በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ የግሉ ዘርፍ ሚና መጎልበት እንዳለበት በማመን እየሰራች መሆኗም ተገልጿል።

በጉባኤው ከኢትዮጵያና አሜሪካ የንግድ መሪዎችና ባለሃብቶች፣ ግዙፍ የአሜሪካ ኩባንያዎች፣ ተዕእኖ ፈጣሪ ኢንቨስተሮችና በጎ አድራጊዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ቅድሚያ በሰጠቻቸው የንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ይገኛሉ ተብሏል።

በኢትዮጵያና አሜሪካ የሚገኙ ባለሃብቶች፣ ስራ ፈጣሪዎችና በጎ አድራጊዎች  የበለጸገች፣ ደህንነቷ የተጠበቀና ቀጣይነት ያለው እድገት የምታስመዘግብ ኢትዮጵያን እውን በማድርግ ሂደት ይወያያሉ።

ጉባኤው የአዲስ ምዕራፍ ጅማሮ ማብሰሪያ ሲሆን ግቡም ሁለቱ አገሮችን ከዚህ ተጠቃሚ ማድረግ መሆኑን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም