በግብርናው ዘርፍ አሁን ባለው አሰራር የታሰበውን ለወጥ ማምጣት አይቻልም ተባለ

72

አዲስ  አበባ ግንቦት  1/2011 በግብርናው ዘርፍ አሁን  ባለው  አስራር  ብቻ  የታሰበውን የትራንስፎርሜሽን ግብ ማሳካት እንደማይቻል የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ ገለጹ::

የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ በግብርና ትራንስፎርሜሽን ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማካሄድ  ጀምሯል።

የቢሮው ሃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት "የክልሉም ሆነ የሀገሪቷ የግብርና አሰራር አሁን ባለው ጥቃቅን ለውጥ ብቻ ታግዞ የታሰበውን የትራንስፎርሜሽን ግብ ማሳካት አይችልም"።

የክልሉ ግብርና ቢሮ በዘርፉ የሚሰሩ 54 ተመራማሪዎችን በማሳተፍ ግብርናውን ለማዘመን ያለመ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ላይ ይገኛል።

ጥናትና ምርምሩ ያተኮረው በ9 የተለያዩ የግብርናው ዘርፍ ግብአት፣አሰራርና አጠቃቀም ዙሪያ ላይ ያተኮረ መሆኑን ሃላፊው አብራርተዋል።

በግብርና ግብአት እጥረት፣ በመስኩ ላይ ስለሚሰሩ ተቋማት፤ የግብርና ሜካናይዜሽን፤ የመኖ አጠቃቀም፤ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም፤ ስለመስኩ ጥናትና ምርምር እጥረቶች፤ አጠቃላይ የግብርና ኤክስቴንሽን አተገባበር፤ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የግብርና ኮሜርሻላይዜሽን የጥናቱ የትኩረት መስኮች ናቸው።

በውይይቱ  ቀደም ብለው የተጠናቀቁትን ጥናቶች ስራ ላይ ለማዋልና ግብርናን በታሰበው ልክ ለማዘመን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተጨማሪ ሃሳቦችን ለማግኘት መሆኑ ተገልጿል።

የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴንና የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል የግብርና ሃላፊዎችና የዘርፉ ተመራማሪዎች በውየይቱ ላይ ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም