በዘንድሮው ክረምት 4 ቢሊዮን ችግኝ ይተከላል-የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን

162

ሚያ  30/2011 በዘንድሮው የክረምት ወቅት 4 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራ የሚኒስትሮች ኮሚቴ መቋቋሙ ተገለጸ።

የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳሬክተር አቶ ተስፋዬ ጋሻው ለኢዜአ እንደገለጹት በመጪው የክረምት ወቅት ብሔራዊ የደን ልማት ንቅናቄ የችግኝ ተከላ(green campaign) ይከናወናል።

ለተከላውም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ዳይረክተሩ፤ ተከላው  ከሐምሌ አጋማሽ ጀምሮ እስከ ጵግሜ ድረስ የሚከናወን ይሆናል።

በብሔራዊ ደረጃ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራና የተለያዩ ዘርፎችን የሚመራ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ዓላማውን በበላይነት እንዲመራ ተመስርቷል።

ከብሔራዊ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስር በአካባቢ፣ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የቴክኒክ ኮሚቴ መቋቋሙንም ገልጸዋል።

እንደ ዳሬክተሩ ገለጻ፣ የንቅናቄው ዓላማ በችግኝ የመጽደቅ ምጣኔ ላይ እያጋጠሙ  ያሉ ችግሮችን በመቀነስ ማህበረሰቡ የሚተክለውን ችግኝ በባለቤትነት እንዲንከባከብ ግንዛቤ መፍጠሪያ ስራም የሚሰራበት ነው።

በብሔራዊ ደረጃ ለሚተከለው 4 ቢሊዮን ችግኝ በመንግስት ችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች የተለያዩ የዛፍ ዝርያዎች 3 ቢሊዮን ችግኝ እየፈላ የሚገኝ ሲሆን 1 ቢሊዮን ችግኝ ደግሞ ከግል ጣቢያዎች እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ለንቅናቄው መሳካት የፌዴራልና የክልል ተቋማት እንዲሁም የግል ተቋማትም በትብብር የሚሰሩ ይሆናል።

ንቅናቄው በሁለተኛው የአድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አንድ ሚሊዮን ሔክታር በደን ለመሸፈን የተያዘውን እቅድ ለማሳካት እንደሚያግዝም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም