በበጀት ዓመቱ አስር ወራት ወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ የተያዘው እቅድ አፈጻጻም ዝቅተኛ ነው— ሚኒስቴሩ

1412

ሀዋሳ  ግንቦት 28/2010 በበጀት ዓመቱ አስር ወራት ወጣቶችን  በቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ የተያዘው እቅድ አፈጻጻም ዝቅተኛ መሆኑን የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስትሩ ያለፉትን ወራት አፈጻጸም የሚገመግም መድረክ በሃዋሳ እያካሄደ ነው፡፡

ሚኒስትሩ አቶ ርስቱ ይርዳ በመድረኩ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ ሁለት ሚሊዮን 800 ሺህ ወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ነበር፡፡

” ባለፉት አስር ወራት የስራ እድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች ግን አንድ ሚሊዮን 700ሺህ  ብቻ በመሆናቸው አፈጻጻሙ ዝቅተኛ ነው” ብለዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ በሃገሪቱ የተከሰተው አለመረጋጋት በኢኮኖሚው ዘርፍ ተገቢውን ስራ እንዳይከናወን ተጽዕኖ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡

የአስፈጻሚ አካላት ትጋት ማነስ፣ አመራር ለውጥና ቅንጅታዊ አሰራር ጉድለትም ተገቢውን ውጤት እንዳይመዘገብ ማድረጉ ሌላው ክፍተት እንደሆነ ነው የተመለከተው፡፡

በወጣቶች በኩልም በአመለካከት ረገድ የሚስተዋሉ ችግሮች መኖራቸውንና በተገኘው ስራ በመሰማራት በኩል ያለውን ውስንነት መፍታት የማህበረሰቡም ሊሆን ይገባል ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡

በመንግስት የተመደበው የተዘዋዋሪ የብድር ገንዘብ አቅርቦትና ስርጭት ባለፉት ሶስት ወራት መሻሻሎች ቢኖርም ክፍተቶች መስተዋላቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የብድሩ ገንዘብ በመጠቀም ረገድ በክልሎች የተደራጁ ሪፖርቶች ያለመቅረብና  በፌደራል መንግስቱም ገንዘቡን በመልቀቅ ረገድ የነበሩ መዘግየቶች ሚኒስትሩ የጠቀሷቸው ናቸው፡፡

” እስካሁን ሰባት ቢሊዮን 800 ሚሊዮን  ብር ለክልሎች ተሰራጭቷል ” ያሉት ሚኒስትሩ ቀሪው ገንዘብ በቀጣይ እንደሚሰራጭና አፈጻፀሙን በቅርበት የመከታተል ስራ እንደሚከናወን ገልጸዋል፡፡

ባለፉት አስር ወራት 196ሺህ 44 ወጣቶችን በቋሚና ጊዜያዊ ገጠር ስራ እድል ተጠቃሚ እንደሆኑ ማመቻቸቱን የገለጸው ደግሞ የደቡብ ህዝቦች ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ  ነው፡፡

አፈጻጻሙ ከእቅዱ አንጻር 56 መቶ መሆኑን በቢሮው  የገጠር ስራ እድል ፈጠራ ኤጄንሲ ስራ አስኪያጅ አቶ ኢዘዲን ሙስባህ ተናግረዋል፡፡

በቁጥር ደረጃ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ ቢሆንም በጥራት ካለፉት ዓመታት የተሻለ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የአማራ ክልል ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ በላይ ዘለቀ በበኩላቸው በተዘዋዋሪ ብድር ገንዘብ  31ሺ ወጣቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በሁለት ዙር የተለቀቀላቸውን ተዘዋዋሪ የብድር ገንዘብ ማሰራጨታቸውንም ተናግረዋል፡፡

በአርብቶ አደር አካባቢ ያለው የስራ ባህል ባለማደጉ ባቀዱት ልክ አለመከናወኑን የተናገሩት ደግሞ የአፋር ክልል ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ማኢር አሊሲሮ ናቸው፡፡

በበጀት ዓመቱ ከ33ሺ በላይ ወጣቶችን በቋሚና ጊዜያዊ ስራ እድል ለማሰማራት አቅደው እስካሁን ወደ ስራ የገቡት 11ሺ 700 ብቻ ናቸው፡፡

በመድረኩ የየክልሎቹና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ያለፉት አስር ወራት  አፈጻጸም እየተገመገመ ሲሆን ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመለየት ለቀጣይ ዓመት አቅጣጫ እንደሚቀመጥም ይጠበቃል፡፡