ባለሃብቶች በእንጨት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ልማት በመሳተፍ የውጭ ምርቶችን መተካት ይጠበቅባቸዋል

62


መቐለ ሚያዚያ 29 / 2011 ባለሃብቶች በእንጨት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ልማት በመሳተፍ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት ይገባቸዋል ተባለ።

በአገሪቱ የእንጨት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ልማት በሚስፋፋበት ሁኔታ የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ከኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት በመተባበር ዛሬ በመቐለ የምክክር መድረክ አካሂዷል።

በምክክር መድረኩ ላይ የክልሉ ንግድ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳንኤል መኮንን በዚሁ ወቅት እንዳመለከቱት የአገራችን ባለሃብቶች የተለያዩ የእንጨት ውጤቶችን ከውጭ ከማስገባት በአገር ውስጥ የሚያመርቱበት ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል።

ባለሃብቶቹ በመስኩ ቢሰማሩ ከሚፈጥሩት ሥራና በግላቸው ከሚያገኙት ገቢ በተጨማሪ አገሪቱ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት ይችላሉ ብለዋል።

ዘርፉን ለማሳደግ መንግስትና ባለሃብቶች ተቀራርበው መስራትና በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ማስወገድ እንደሚቻል አቶ ዳንኤል አስረድተዋል።

የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ አቶ ሃፍቱ ሐጎስ የአገሪቱ የደን ልማት ሃብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ባለመዋሉ ከውጭ ምንዛሪ የእንጨት ውጤቶች እያስገባች መሆኗን አስረድተዋል።

መንግሥት በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች የተለያዩ የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ቢያደርግላቸው በብዛት ለማስገባት ያግዛል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለእንጨት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ልማት የሚሆን ሰፊ የተፈጥሮ ሃብት ያላት ቢሆንም ባለሃብቶች ወደዚሁ ዘርፍ ለመግባት ያላቸው ፍላጎት አነስተኛ መሆኑን የቀረበው ጥናት አመልክቷል።

የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ሊቀመንበርና የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አሰፋ ገብረሥላሴ መድረኩ ባለሃብቶች፣የምርምር ተቋማትና የግብርና ባለሙያዎች የተፈጥሮ ሃብትን ጥቅም ላይ ለማዋል ስለሚቻልበት ሁኔታ ግንዛቤ ለመፍጠር መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

መድረኩ በትግራይ፣በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች እንደሚካሄድ አስረድተዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ፍስሃ ከበደ በሰጡት አስተያየት ዘርፉ ትኩረት ሳያገኝ መቆየቱን አስታውሰው፣ መድረኩ ዘርፉ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በማንቀሳቀስ ያለውን  ፋይዳ እንዳመለከታቸው ተናግረዋል።

በመድረኩ በእንጨት ስራ የተሰማሩ ባለሃብቶች፣የፌዴራል ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና አግባብ ካላቸው ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም