የማጃንግ ጥቅጥቅ የደን ሀብት ጠብቆ ለማቆየት የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ሥራ መጠናከር እንዳለበት ተጠቆመ

54


ጋምቤላ ሚያዝያ 29 / 2011 በጋምቤላ ክልል በዓለም ከባቢያዊ ሕይወት ጥበቃ የተመዘገበውን የማጃንግ ጥቅጥቅ የደን ሀብት ጠብቆ ለማቆየት የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ሥራ መጠናከር እንዳለበት ተጠቆመ

ደኑን ከሚያጋጥሙት ችግሮች ለመጠበቅ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ የክልልና የማጃንግ ዞን ከፍተኛ አመራሮች ትናንት በጋምቤላ ከተማ ተወያይተዋል።

በከባቢያዊ ሕይወት ጥበቃ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ተፈጥሯአዊና ሰው ሰራሽ ችግሮችን ለመከላከልና ደኑ ተጠብቆ ለማቆየት ዘርፉ የሚመለከታቸው አካላት ቅንጅታዊ ሥራ መጠናከር እንዳለበት የውይይቱ ተሳታፊዎች አመልክተዋል፡፡

በተለይም በአካባቢው የሚካሄደው የእርሻ ኢንቨስትመንት፣ ከሰል ማክሰልና የማገዶ እንጨት ፍለጋ በደኑ ላይ ጉዳት እንዳያመጣ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ቤል ኬት እንዳሉት በከባቢያዊ ሕይወት ጥበቃ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በደኑ ላይ ጉዳት እንዳያስከትል ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ብለዋል።

በተለይም የክልሉ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ፈቃድ ከመስጠቱ በፊት የአካባቢ ተፅዕኖ ጥናት ሊያደርግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ከዚህም ባሻገር በአካባቢው የሚካሄደው የጣውላ ሥራና የማገዶ እንጨት ፍለጋ የደን መመናመን ስለሚያስከትል መንግሥት ጥበቃ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

ደኑን ጠብቆ ለማቆየት ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን በማዘጋጀት ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን መመቻቸት እንዳለበትም ተናግረዋል።

አቶ ገዛኸኝ ገብረሚካኤል የተባሉ ተሳታፊ በበኩላቸው የደን ሀብቱን በዘላቂነት ለመጠበቅና ለመንከባከብ ጉዳት የሚያደርሱ አካላት በህግ የሚጠየቁበት ሁኔታ መፈጠር አለበት ብለዋል።

በተጨማሪም በአካባቢው በቡና ልማት ላይ የሚሰማሩ አርሶ አደሮች በደኑ ላይ ጉዳት እንዳያስከትሉ የግብርና ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን መስጠት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በክልሉ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት በተለይም የክልሉ አካባቢ፣ደንና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ፣ የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ፣ኢንቨስትመንት ኤጀንሲና አግባብ ያላቸው አካላት ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

እንደ ችግር የተለዩትን ነጥቦች እንደ ግብዓት በመውሰድ በቀጣይ  በጋራ መሥራት ይገባናል ያሉት ደግሞ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ ዶክተር ሎው ኡቡፕ ናቸው።

በተለይም በክልሉ በበጋው ወቅት የሚስተዋለው የደን ቃጠሎ በከባቢ ሕይወት ጥበቃ ላይ ችግር እንዳይፈጥር ከአካባቢው ማህብረሰብ ጀምሮ ሁሉም ድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተንኳይ ጆክ እንዳሉት መንግሥት የክልሉን የተፈጥሮ ሀብት ተጠብቆ እንዲቆይ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ ነው።

በተለይም የማጃንግ ጥቅጥቅ ደን ከጉዳት ለመጠበቅ የክልሉ መንግስት እንደ መልካ ኢትዮጵያ ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ለመጠበቅ እያንዳንዱ ሴክተር መስሪያ ቤት በተለይም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡ አሳስበዋል።

የማጃንግ ዞን ጥቅጥቅ የደን ሀብት በ2010 በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፡የሳይንስና የባህል ድርጅት( ዩኔስኮ) ተመዝግቧል፡፡

ደኑ በውስጡም ከ550 በላይ የዕፅዋት ዝርያዎች፣33 አጥቢ እንስሳት፣130 የአዕዋፍ ዓይነቶችና 20 ተሳቢ የእንስሳት ዝርያዎች እንደሚገኙበት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም