ለእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ ግንባታ እየተከናወነ ነው

58

ባሀር ዳር ሚያዝያ 29/2011 የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎችን የቅበላ አቅም ለማሳደግ በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ ግንባታ እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ጋርዳቸው ወርቁ ለኢዜአ እንደገለጹት ካለፈው ዓመት ጀምሮ እየተካሄደ ያለው ግንባታ 85 በመቶ ተጠናቋል።

ከመጋቢት ወር 2010 ጀምሮ  እየተካሄደ ባለው ግንባታ ሶስት የተማሪ መኝታ ህንፃዎችን ያካትታል፡፡

ዪኒቨርሲቲው በሚቀጥለው የትምህርት ዘመን 2ሺህ 160 አዲስ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር እንደሚያስችለውም አስታውቀዋል።

በዚህም በባለአራት ወለል ከፍታ ያላቸው ህንጻዎች ህግና ጤናን ጨምሮ አምስት ተጨማሪ የትምህርት ክፍሎችን ለመክፈት ያስችሉታል ብለዋል።

ከማስፋፊያ ግንባታው በተጓዳኝም በአ200 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ በጀት እየተገነቡ ካሉት የግቢ መሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች በከፊል መጠናቀቃቸውን ዶክተር ጋርዳቸው ገልጸዋል።

ከተጠናቀቁት ውስጥም ዩኒቨርሲቲው ራሱን ችሎ ያስገነባው የንፁህ መጠጥ ውሃ ለ24 ሰዓት ያለማቋረጥ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፣ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታም ይገኙበታል።

እንዲሁም የዘጠኝ ኪሎ ሜትር የውሃ ማፋሰሻ ቦይና የዘጠኝ ኪሎ ሜትር የኮንክሪት አስፋልት መንገድና የድንጋይ ንጣፍ መንገዶች  እየተጠናቀቁ መሆናቸውን ምክትል ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል።

የወርቅነህ ጉዳይ ስራ ተቋራጭ ጀኔራል ፎርማን አቶ መስፍን ታደሰ በበኩላቸው የተማሪዎች ማደሪያ የማስፋፊያ ህንፃ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን  አስታውቀዋል።

ዩኒቨርሲቲው ሥራ ከጀመረበት ከጥር 2010  ጀምሮ እስካሁን ከ2 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎች እያስተማረ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም