ከ100 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው መመለሳቸው ተገለጸ

100

ሚያዝያ 28/2011 የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በዚህ ወር ከመቶ ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው መመለሱን አስታወቀ።

ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ አካባቢያቸው ለመመለስና መልሶ ለማቋቋም በተከናወነ ተግባር 112 ሺህ 652 ዜጎች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን ኮሚሽኑ ለኢዜአ ገልጿል።

ተፈናቃዮችን ለመመለስ በሚደረገው ጥረት መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አጋር አካላት ሚና የጎላ ነው ብሏል።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ለኢዜአ እንደገለጹት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በግጭት ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ እየተደረገ ነው።

ከድጋፉ ባሻገር ወደ ቀዬአቸው የመመለስና መልሶ የማቋቋም ስራውም እንዲሁ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

ተፈናቃዮቹ ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ ቀደም ሲል የነበራቸውን የኑሮ ሁኔታ ለመመለስ የሚያስችል ስራዎችን ከአጋር አካላት ጋር በትብብር እየሰራን ነው ያሉት ዳይሬክተሩ የቤት መስሪያ፣ የውሃ፣ የትምህርትና የጤና አገልግሎቶች እየተሟላላቸው ነው ብለዋል።

ከተመለሱ በኋላም እስኪቋቋሙ ከስድስት ወር እስከ አንድ አመት ባለው ግዜ የሚደረግላቸው መሰረታዊ ድጋፎች በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በጌዴኦና ምእራብ ጉጂ ዞን ተፈጥሮ በነበረው ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ በተደረገው ጥረት እስካሁን 15 ሺህ ተፈናቃዮች ተመልሰዋል።

ለተመለሱት ተፈናቃዮች መጠለያ በመስራት ረገድም 10ሺህ የቤት መስሪያ የፕላስቲክ ቁሶችና 30 ሺህ ቆርቆሮ መገዛታቸውን ጠቁመው መጠለያው በአካባቢው ማህበረሰብና በአጋር አካላት አማካኝነት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

ከአማራ ክልል ከማእከላዊና ምእራብ ጎንደር ዞኖች ደግሞ ከ18 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች መመለሳቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ  የአካባቢው ማህበረሰብ መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ርብርብ የጎላ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

በዚህም ከ250 ሺህ በላይ ቆርቆሮ በድጋፍ መበርከቱንና ይህም የዜጎችን የመደጋገፍና የመረዳዳት ባህል የሚያጎለብት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ከኦሮሚያ ክልል ምእራብና ምስራቅ ወለጋ ዞኖች ከተፈናቀሉ 178 ሺህ ዜጎች ውስጥ እስካሁን 55 ሺህ ዜጎች ተመልሰዋል።

በተጨማሪም ከደቡብ ክልል ከተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች የተፈናቀሉ ዜጎችም እንዲሁ ወደ አካባቢያቸው እየተመለሱ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህ ደግሞ የአገሪቱን ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ እየተሰራ ካለው ስራ ባሻገር በሃይማኖት አባቶች፣ በአገር ሽማገሌዎች፣ በአባ ገዳዎችና የየክልሉ ፕሬዝዳንቶች በህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና ትስስር ላይ እያከናወኑ ያሉት ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው ነው ያሉት።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብና ትግራይ ክልሎች የሚገኙ ተፈናቃይ ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ የሚቃኝ 24 አባላት ያለው ቡድን ተዋቅሮ የመስክ ምልከታ ማድረጉና የምልከታውን ውጤት ሪፖርት ሚያዚያ 25 ቀን 2011 ዓ.ም ማቅረቡ ይታወቃል።

አባላቱ በአራቱ ክልሎች የሚገኙ 27 መጠለያዎቸን እንደጎበኙና ተፈናቃይ ዜጎች በቂ እርዳታ እየተደረገላቸው አለመሆኑንና ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች እየተዳረጉ መሆኑን አብራርተዋል።

በዋናነትም ተፈናቃዮችን መልሶ የማቋቋም ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥልና የችግሩ መንስኤ የሆኑ አካላትን በአስቸኳይ ተጠያቂ የማድረግ ስራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም