ፕሮሶፒስ አረም ስጋትነቱ ሊያከትም ነው…የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል

122

ሚያዝያ  28//2011 በአፋር ክልል ብቻ 1ነጥብ 3 ሚሊዮን ሔክታር የግጦሽ መሬት የወረረው ፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ የተባለው መጤ አረምን የሚያስወግድ መፍትሔ ማግኘቱን የወረር ግብርና ምርምር ማእከል አስታወቀ ።

የማእከሉ ተወካይ አቶ አሸናፊ ወርቁ እንደገለፁት ፕሮሶፒስ ጂሊፍሎራ የተባለው መጤ    አረም የተፈጥሮ ግጦሽ መሬትን በመውረር አርብቶ አደሩን ለችግር ሲያጋልጥ ቆይቷል ።

ተክሉ በ1970ዎቹ መጀመሪያ በረሃማነትን ለመከላከልና እርሻዎችን ከአቧራና ከአውሬ ለመጠበቅ እንደ አጥር ያገለግላል ተብሎ ወደ አገራችን የገባ ነው ተብሏል ።

በሒደት በአሳሳቢ ሁኔታ በመስፋፋት በአፋር 1ነጥብ 3 ሚሊዮን ሔክታር ፣ በአጎራባች የኦሮሚያ አካባቢዎች ፣በድሬዳዋና በሶማሌ ክልል ደግሞ ሰፊ ግጦሽ መሬት በመውረርና ብዝሃ ህይወትን በማጥፋት አርብቶ አደሩን ለድርቅ ተጋላጭ ማድረጉን ተናግረዋል።

መንግስት ፣ በየደረጃው የሚገኙ የአስተዳድር መዋቅሮችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት መጤ አረሙን አሳሳቢነት በመገንዘብ በጋራና በተናጠል ለማጥፋት ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ መቆየቱን አስረድተዋል ።

“የኋላ ኋላ የተሻለ አማራጭ ሆኖ የተገኘው አረሙ በሰው ጉልበት እየተነቀለ እንዲቃጠል ማድረግቢሆንም በጊዜ ፣ በጉልበትና በወጪ ደረጃ አዋጪ ሆኖ አልተገኘም”ብለዋል ።

የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል አማራጭ ቴክኖሎጂዎችን በማፈላለግ ካቪ ከተባለ ዓለም አቀፍ የምርምር ማእከል ጋር በመተባበር ከደቡብ አፍሪካ ሁለት የኬሚካል ዓይነቶችን በማስመጣት ባለፉት ዓመታት በተግባር በመሞከር ውጤታማ መሆናቸውን አረጋግጧል ።

“በአንድ ሔክታር መሬት የሚገኝ ፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ አረም በሰው ጉልበት ለመንቀል ከ20 እስከ 30 የሚደርሱ ሰዎች በማሰማራት እስከ አራት ቀናት ድረስ የሚጠይቅ ሲሆን በኬሚካሎቹ ግን በቀን አንድ ሰው እስከ 5 ሔክታር ማዳረስ ይችላል”ብለዋል ።

ከወጪ አንፃርም ቢሆን በሰው ጉልበት አረሙን ከአንድ ሔክታር ለማስወገድ ከ9 እስከ 13 ሺህ ብር የሚጠይቅ ሲሆን በ12 ዶላር በሚገዛ ኬሚካል ግን 5 ሔክታር መሬት ከአረሙ ነፃ ማድረግ እንደሚቻል አቶ አሸናፊ አስረድተዋል ።

“አንደኛው ኬሚካል የወራሪው አረም ስር እስከ 15 ሳንቲሜትር ከፍታ   ድረስ በመርጨት ፣ ሁለተኛው ኬሚካል ደግሞ አረሙን ከታች ቆርጦ በመቀባት በቀላሉ ማስወገድ እንደሚቻል በተግባር ተረጋግጧል”ብለዋል ።

“ኬሚካሎቹ አረሙን በመጀመሪያው አምስት ቀናት ብጫ መልክ እንዲይዝና    በ15ቀናት ውስጥ ደግሞ በማድረቅ እንዲጠፋ የማድረግ አቅም አላቸው” ብለዋል ።

በኬሚካሎቹ እንዲወገድ የተደረገው አረም መልሶ ያቆጠቁጥ እንደሆን   ባለፉትሁለት ዓመታት ሁለት የዝናብ ወቅቶችን ተጠብቆ ማረጋገጥ እንደተቻለው በምንም መልኩ አረሙ ተመልሶ ህይወት የመዝራት አቅም እንዳላገኘ አቶ አቶ አሸናፊ ተናግረዋል ።

አረሙ በእንስሳት ላይ ጉዳት ካደረሰባቸው የአፋር ክልል ነዋሪዎች መካከል በአሚባራ ወረዳ የወረር አካባቢ አርብቶ አደር መሀመድ ሁሴን አንቱታ በሰጡት አስተያየት አረሙ በአካባቢያቸው የነበረው የግጦሽ ሳርና ለመኖነት የሚያገለግሉ እፅዋት አጥፍቷል።

ከዚህም ባሻገር የአረሙ እሾህ የቤት እንሰሳትን በመውጋት ዓይናቸው እንዲጠፋ ፣ እግራቸው እንዲያነክስና መንጋጋቸው እንዲጣመም በማድረግ ጉዳት እያደረሰባቸው መሆኑን ገልፀዋል ።

የወረር ግብርና ምርምር ማእከል አሁን የጀመረው አረሙን በኬሚካል የማጥፋት ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥልም አርብቶ አደሩ ጠይቀዋል ።

የአፋርዋ ሴት አርብቶ አደር ፋጡማ ዓሊ በበኩላቸው መጤው አረም በቅርቡ 15 በግና ፍየሎች እንደገደለባቸው ገልፀው ኬሚካሉ በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውል ጠይቀዋል ።

ከኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በአሁኑ ጊዜ በአገራችን 35 አዲስ ወራሪ መጤ ዝርያዎች ይገኛሉ ።

በሚያስከትሉት ተፅእኖ መጠን ክትትል ፣ ቁጥጥርና የማስወገድ ልዩ ትኩረት የተሰጣቸው አራቱ ዋና ዋና መጤ ወራሪ አረሞች ደግሞ ፈረምሲሳ ፣ ፕሮሶፒስ ፣ እምቦጭና የወፍ ቆሎ የተባሉት ናቸው ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም