ተመራቂዎች ያገኙትን እውቀት በተግባር በመተርጎም የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ማቃለል ይገባቸዋል- የኦሮሚያ ጤና ቢሮ

91

አዳማ ሚያዝያ 27/2011 ተመራቂዎች ዕውቀታቸው በተግባር በመተርጎም የህብረተሰቡን የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ማቃለል እንደሚገባ የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ አሳሰበ። 

የአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ በተለያዩ የሙያ መስኮች ለአራተኛ ጊዜ  ያሰለጠናቸውን 135 የህክምና ዶክተሮችና የጤና መኮንኖች ዛሬ አስመርቋል።

የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በምረቃው መርሃ ግብር ላይ እንደገለጹት ከህብረተሰቡ  የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ቅሬታዎችን ለመመለስና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ተመራቂ ባለሙያዎች ያገኙትን እውቀት በተግባር መተርጎም ይጠበቅባቸዋል።

"ፍትሃዊና ቀልጠፋ አገልግሎት ማግኘት ህብረተሰቡ ከጤና ባለሙያዎች የሚጠብቀው ግንባር ቀደም ምላሽ ነው ''ያሉት ኃላፊ፣ በህክምናው ዘርፍ የሚስተዋለውን የሰው ኃይል ክፍተት ለመሙላት የክልሉ መንግስት በሙሉ አቅሙ እየሰራ ነው ብለረዋል።

የባለሙያዎችን የትምህርት ደረጃ ማሻሻልና እውቀታቸውን የመገንባት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተው፣ "የዛሬው ምረቃት በጤናው ዘርፍ እየተከናወነ ያለው ሪፎርም እንዱ አካል ነው" ብለዋል።

ኮሌጁ አገልግሎቱን ለመስጠት እንዲያስችለው የክልሉ መንግስት በመደበው ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ከ600 በላይ ህሙማንን አስተኝቶ የሚያሳክሙ አልጋዎች የተሟሉለት ሆስፒታል በመገንባት ለአገልግሎት ማብቃቱን ጠቅሰዋል። 

የጤናውን ዘርፍ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታትየጥናትና ምርምር ሥራዎችን ጨምሮ የሰው ሃይል አቅም ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ዶክተር ደረጀ ተናግረዋል።

የአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ በአዲስ መልክ በመገንባት፣ በቁሳቁስና በሰው ኃይል በማደራጀት ዘመናዊ የህክምና ማዕከል እንዲሆን መደረጉንም ገልጸዋል።

ተመራቂ ሙያተኞችን ወደ ሥራ ለማሰማራት ዝግጅት መደረጉን የተናገሩት ኃላፊው፣ ተመራቂዎች ህብረተሰቡን በቅንነትና በተማኝነት ማገልገል እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

የአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መኮንን ፈይሳ በበኩላቸው ኮሌጁ ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ በጤና ችግሮች ላይ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን እያከናወኑ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በስነ ተዋልዶ፣በህብረተሰብ ጤና፣ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች፣በአገልግሎት ማሻሻያ ዙሪያ የተካሄዱ የጥናትና ምርምር ውጤቶች በክልሉ የጤና ተቋማት እየተካሄደ ላለው ሪፎርም ግብዓት ሆነው እንደሚያገለግሉ አስረድተዋል።

ኮሌጁ ከትምህርትና ስልጠና በተጨማሪ ተገልጋዩ ማህበረሰብ ፍትሃዊና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት አሰራሩን እያሻሻለ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኮሌጁ በቀዶ ጥገና፣በማህጸንና ጽንስ፣ በጠቅላላ ህክምና ስፔያላይዜሽን፣በህብረተሰብ ጤና፣በስነ ተዋልዶ፣በሰመመን ሰጪነት ያሰለጠናቸውን የህክምና ዶክተሮችና የጤና መኮንኖች ዛሬ ለምረቃ ማብቃቱንም ተናግረዋል።

ከተመራቂዎቹ መካከል 53 የሚሆኑት የህክምና ዶክተሮች ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ የጤና መኮንኖች ናቸው ።

ከተመራቂዎቹ መካከል ዶክተር ሳምራዊት ተፈሪ በስልጠና ቆይታዋ ያገኘችውን እውቀትና ክህሎት ወደ ተግባር በመየቀር የተገልጋዮች እርካታ ለማምጣት በሙሉ አቅሟ እንደምትሰራ ቃል ገብታለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም