በታህታይ አዲያቦ ወረዳ ከ81 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የውሃ ማሸጊያ ፋብሪካ ተመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
በታህታይ አዲያቦ ወረዳ ከ81 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የውሃ ማሸጊያ ፋብሪካ ተመረቀ
ሽሬ እንዳሥላሴ ሚያዝያ 27/2011 በትግራይ ክልል ታህታይ አዲያቦ ወረዳ በአንድ ባለሃብት በ81ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የተጣራ ውሃ ማሸጊያ ፋብሪካ ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት በቃ።
ፋብሪካው በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን በታህታይ አዲያቦ ወረዳ ልዩ ስሙ “ማይ ማፃ” በተባለ ስፍራ የተገነባ ሲሆን፣ ከ100 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ቋሚ የስራ እድል ፈጥሯ።
የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ አቶ ክብሮም መሐሪ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት ግንባታው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የተጠናቀ ሲሆን ፋብሪካ በሰዓት 45 ሺህ 500 ሊትር ውሃን የማምረትና የማጣራት አቅም አለው።
ቋሚ የስራ እድል ከተፈጠረላቸው የፋብሪካው ሰራተኞች መካከል ገሚሶቹ የአካባቢው ወጣቶች መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ፋብሪካውን መርቀው የከፈቱት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተክላይ ገብረመድህን ፋብሪካው በዞኑ ያለውን የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ ለመጠቀም በር መከፈቱን ገልጸዋል።
በዞኑ ያለው የእንስሳት ሃብት ፣ ሰሊጥ ፣ የማዕድን ሃብትና ቱሪዝም ለኢንቨስትመንት ምቹ በመሆናቸው ሌሎች ባለሃብቶች ይህንን እድል እንዲጠቀሙ ጥሪ አስተላለፈዋል።
የፋብሪካው ባለቤት አቶ መሃሪ ፍስሃ በበኩላቸው በፋብሪካውን ግንባታ ወቅት የአካባቢው ነዋሪና አመራሩ ላደረጉላቸው ትብብር አመስግነዋል።
ተገቢ የካሳ ክፍያ ተከፍሏቸው በፋብሪካው ቋሚ የስራ እድል እንዳገኙ የገለጹት ወይዘሮ ህይወት ተስፋማርያም “ብቻዬን ስጠቀምበት የነበረው መሬት ሌሎች ከ100 በላይ ሰዎች ተጠቃሚ ያደረገ ፋብሪካ በመገንባቱ ደስታ ተሰምቶኛል" ብለዋል።
አቶ ፍስሃ በየነ የተባሉ ሌላው የአከባቢው ነዋሪና የልማት ተነሺ አርሶ አደር በበኩላቸው አካባቢው በመልማቱና ሁለት ልጆቻቸው በፋብሪካው ሥራ እድል በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።