”ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ለኦሮሞ ብሎም ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ነጻነትና እኩልነት የታገሉ ታላቅ መሪ ነበሩ ”-የደምቢ ዶሎ ከተማ ነዋሪዎች

188

ነቀምቴ ሚያዝያ 27/2011 በቀድሞ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ለኦሮሞ ብሎም ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ነጻነትና እኩልነት የታገሉ ታላቅ መሪ እንደነበሩ የደምቢ ዶሎ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

የቀድሞው ፕሬዚዳንት የትውልድ ከተማ ነዋሪዎች የተሰማቸውን ጥልቅ ኅዘንም  ገልጸዋ።

ከነዋሪዎቹ አንዳንዶቹ ለኢዜአ እንደተናገሩት የዶክተር ነጋሶ ህልፈተ ሕይወት ለኦሮሞና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ”ትልቅ ጉዳት” ነው።

ከከተማው ነዋሪዎች መካከል የ05 ቀበሌ ነዋሪው አቶ ፋንታ ከበደ ዶክተር ነጋሶ በሕይወት ዘመናቸው ለኦሮሞና ለኢትዮጵያ ሕዝብ መብትና ነፃነት መከበር የታገሉ መሪ እንደነበሩና ህልፈታቸውም አገሪቷን ታላቅ ምሁር አሳጥቶታል ብለዋል፡፡

ሌላው የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ተመስጌን ታደሰ ዶክተር ነጋሶ በሕይወት ዘመናቸው ለኦሮሞና ለአገሪቱ ሕዝቦች መብት መከበር ደከመኝ፣ሰለቸኝ ሳይሉ በሙሉ አቅማቸውና ዕውቀታቸው አገልግሎት የሰጡ መሪ ሲሉ ገልጸውላቸዋል።

የቄለም ወለጋ ዞን የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(ኦዲፒ) የከተማ አደረጃጀት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ስርኔሣ በበኩላቸው ዶክተር ነጋሶን ’’የኦሮሞ ሕዝብ ማንዴላ ነው ቢባል አያሳፍርም”ይላሉ።

በአገሪቱ ዴሞክራሲ እንዲስፋፋ መስዋዕትነት የከፈሉ ታላቅ መሪ እንደነበሩ ገልጸው፣ለራሳቸው ሳይሆን ለሕዝብ የኖሩ፣የፀና አቋም ያላቸውና በሥነ ምግባራቸው የተመሰገኑት መሪ አርአያነት ምሁራንና በተለይም ወጣቶች እንዲከተሉ ጠይቀዋል።

የደምዶሎ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ታደለ ገመቹ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው በከተማው አስተዳደር ሕዝብና ስም የተሰማቸውን ጥልቅ ኅዘን በመግለጽ ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡

ደምቢ ዶሎ ዶክተር ነጋሶ በ1935 የተወለዱባት ከተማ ናት።