የወንድማማችነትና የአብሮነት እሴቶች ዳግም የሚጠናከሩባቸው መድረኮች ከነገ ጀምሮ በኦሮሚያ ይካሄዳሉ - የክልሉ ኮሙኒኬሽን

126

ሚያዝያ 27/2011 የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የወንድማማችነትና የአብሮነት እሴቶች ዳግም የሚጠናከሩበት ውይይቶች ከነገ ጀምሮ ለሶስት ቀናት በመላው ኦሮሚያ ይካሄዳሉ ሲሉ የክልሉ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አድማሱ ዳምጠው ገለጹ።

የውይይቱ ዋና ዓላማም በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከክልሉ ህዝቦች ጋር በሰላም እንዳይኖሩ የሚደረጉትን ጥረቶች አምክኖ ህዝቦቹን በጋራ ወደ ልማት ተጠቃሚነት ለማምጣት እንደሆነ ተገልጿል።

የኦሮሚያ ክልል  የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አድማሱ ዳምጠው በተለይ ለኢዜአ በሰጡት መግለጫ  በህዝቦች መካከል የኖረውን የወንድማማችነት ስሜት ለማጥፋት፣ ግጭቶችና አለመተማመኖች እንዲኖሩ የሚፈልጉ አካላት አሉ።

በዚህም ባለፉት ጊዜያት ጥቂቶች ለፖለቲካ ቁማር ሲሉ ኦሮሚያን ጨምሮ ከተለያዩ ክልሎች መፈናቀሎችና ግጭቶች እንዲቀሰቀሱ አድርገዋል።

የችግሩን ምንጭ በማጥናት ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የገለጹት ኃላፊው፤  በቅርብ ጊዜያት የህዝብ ለህዝብ መድረኮች ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ከአማራ፣ ከሱማሌ እና ከሐረሪ ክልሎች ጋር ተደርጎ መድረኮቹም አንድነትን በማጠናከሩ ረገድ የተሳኩ ነበሩ ብለዋል። ቀጣዮቹ መድረኮችም የህዝብ ለህዝብ ውይይቶቹ ቀጣይ መሆናቸውን በማውሳት።

የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች ጋር ያለውን የደምና የአጥንት ትስስር የበለጠ ለማጠናርና የአንድነት መንፈስ ለመፍጠርም መድረኩ ወሳኝነት እንዳለው አቶ አድማሱ አንስተዋል።

ህዝቡ ተረጋግቶ ሰላማዊ ህይወቱን አንዲኖር እንዲሁም በቀደመው የአብሮነት እሴቱ እንዲቀጥልና በልማቱ  ተሳትፎ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆንም ይሰራል ብለዋል።

ለፖለቲካ ጥቅማቸው ሲሉ  ጥቂት አደናቃፊዎች በተለያዩ አካባቢዎች የሚነዙትን አሉባልታዎችን በማጋለጥ 'ኦሮሚያ አፈናቃይ ናት' የሚለውን አሉባልታዎች  ሃሰት መሆናቸውን የምናጋልጥበት  መድረክ ይሆናልም ነው ያሉት አቶ አድማሱ።

ለሶስት ቀናት የሚቆየው መድረክ ከነገ ጀምሮ የሚካሄድ ሲሆን ነገ በ19 ዋና ዋና ከተሞች፣ ከነገ በስቲያ ከ300  በላይ በሆኑ ሁሉም የኦሮሚያ ወረዳዎች እንዲሁም በሶስተኛው ቀን ባሉት ከ7000 በላይ ቀበሌዎች የሰላምና የአንድነት ውይይቶቹ እንደሚካሄዱ ተገልጿል።

በተጨማሪም የኦሮሚያ አጎራባች ክልሎች  የውይይቱ ተሳታፊ የሚሆኑ ሲሆን በሁሉም ወንድማማች ህዝቦች መካከል የአንድነትን መንፈስ በማጠናከር ኢትዮጵያ ወደፊት ለምታደርገው የልማት ጉዞ የሚተባበሩበት ነውም ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም