የመንገድ ላይ ትራፊክ አደጋን ለመቀነስ በአሽከርካሪዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ይገባል

2661

አዲስ አበባ ግንቦት 28/2010 የመንገድ ላይ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ በአሽከርካሪዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚገባ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን አስታወቀ።

ከሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎች መካከል 86 በመቶ የሚሆነው በአሽከርካሪዎች ስህተት የሚደርስ መሆኑ ተጠቁሟል።

‘የመንገድ ትራፊክ ደህንነትን ከማረጋገጥ አኳያ አሽከርካሪዎች ላይ ምን መሰራት አለበት?’ በሚል ሃሳብ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።

የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የባለስልጣኑ የመንገድ ደህንነት ትምህርትና ግንዛቤ ዳይሬክተር አቶ ዮሃንስ ለማ እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ለመጣው የትራፊክ አደጋ የአሽከርካሪዎች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት የሚደረጉ ጥናቶች ያረጋግጣሉ።

ለመንገድ ላይ የትራፊክ አደጋዎች መባባስ በአሽከርካሪዎች ላይ የሚደርሱ ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎች አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

‘የአሽከርካሪዎች የትምህርት ዝግጅት ሁኔታ፣ የስነምግባር ጉድለትና የብቃት ማነስ ለዚህ አስተዋጽኦ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ’ ብለዋል።

አሽከርካሪዎቹ ከአንዳንድ የትራፊክ ተቆጣጣሪ ፖሊሶችና አሽከርካሪዎች ጋር ያላቸው ያልተገባ ግንኙነትና ቀጥረው ከሚያሰሯቸው ባለሃብቶች የሚደርስባቸው ጫና የአደጋ ተጋላጭነታቸውን እንደጨመረው ገልጸዋል።

በመሆኑም በአሽከርካሪዎች የሚደርሰው አደጋ ቁጥር ከፍተኛ ስለሆነ ባለድርሻ አካላት እቅዳቸው ውስጥ አካተው በትኩረት እንዲሰሩበት አቶ ዮሃንስ ጠይቀዋል።

በርካታ የትራፊክ አደጋ መመልከታቸውን የሚናገሩት አሽከርካሪ አቶ ተክሌ ሽፈራው እንደሚሉት፤ በዋናነት የተለያዩ አደንዛዥነት ያላቸውን ነገሮች የሚጠቀሙና መጠጥ ጠጥተው ከስነምግባር ውጭ የሚያሽከረከሩ አሽከርካሪዎች ላይ ችግሩ በስፋት ይታያል።

ለአደጋው መባባሰ የአሽከርካሪዎች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ከመግለጽ ባለፈ ለአደጋ የሚያጋልጣቸውን ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮችን በመለየት መፍትሄ ለመስጠት የተደረገው ጥረት አናሳ መሆኑን ጠቁመዋል።

በፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ወልደዮሃንስ በበኩላቸው፤ ከዚህ በፊት በትራፊክ ደህንነት ላይ እያንዳንዱን ችግር በመለያየት ትኩረት ሰጥቶ ያለመስራት ክፍተቶች እንደነበር አስታውሰዋል።

ከዚህ በፊት ስለ ትራፊክ አደጋ የሚሰሩ ስራዎች የአሽከርካሪ ስህተት፣ የመንገድ ደህንነትና የተሽከርካሪ የቴክኒክ ብልሽት ለአደጋው መከሰት ድርሻውን የሚወስዱ ቢሆንም አንዱን ችግር ነጥሎ መስራት ባለመቻሉ ለውጥ እንዳይመጣ ማድረጉን ተናግረዋል።

ለእነዚህ አደጋዎች መበራከት የፍቃድ ሰጭው ክፍተት፣ የማሰልጠኛ ተቋማት ችግር፣ ስርዓተ ትምህርቱ ላይ የሚታዩ ክፍተቶች በዋናነት የሚጠቀሱ ጉዳዮች መሆናቸውን ተናግረዋል ።

በቀጣሪ ባለሃብቶች ሹፌሮች ከጫና ውጪ ሆነው እንዲሰሩና የተሸከርካሪዎች የቴክኒክ ምርመራ በማድረግ የአደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ በትኩረት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

በመሆኑም በአሸከርካሪዎች ስህተት እየደረሰ ያለውን የአደጋ ለመቀነስ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በባለስልጣኑ በኩል ለትራፊክ አደጋ መንስኤ የሚባሉ አሽከርካሪዎችን አቅም ለማሳደግ ስልጠናዎችን በመስጠት ውይይቶችን በማካሄድ ለውጥ ለማምጣት ከባለድርሻ አካላት ጋር መስራት መጀመራቸውን ተናግረዋል።