የኢትዮጵያን ዳግም ውልደት የምናውጅበት ጊዜው አሁን ነው-ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

66

አዲስ አበባ ሚያዚያ 27/2011 አሁን ላይ የኢትዮጵያን ዳግም ውልደት የምናውጅበት ጊዜ ሊሆን ይገባል ሲሉ የኢፌዴሬ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።

78ኛው የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች የድል ቀን ዛሬ ተከብሯል።

በ1928 ዓ.ም የኢጣሊየን ወራሪ ሃይል ከ40 ዓመታት በፊት በአድዋ የደረሰበትን ሽንፈት ለመበቀል ጦርነት በማወጅና ኢትዮጵያን ለመውረር ህዝቡን መርዝ ጋዝ በመታገዝ በግፍ የጨፈጨፈበት ጊዜ ነበር።

በዚህም የኢጣሊያን ቅኝ ገዥዎች ለአምስት ዓመታት ያህል በኢትዮጵያ የቆዩ ቢሆንም ጀግኖች ኢትዮጵያ አርበኞች ግን ወደ መሀል ሀገር የገባውን የኢጣሊያንን ቅኝ ገዥ ድል በማድረግ ነጻነታቸውን አውጀዋል።

ይህ የድል በዓለም በኢትዮጵያ በየዓመቱ ሚያዚያ 27 ቀን ተከብሮ ይውላል።

ይህ የድል ቀን በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ከተማ የድል ሃውልት በሚገኝበት የአራት ኪሎ አደባባይ የኢፌዴሬ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በተገኙበት ተከብሯል።

የኢፌዴሬ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልእክት ኢትዮጵያን ጀግኖች የራሳቸውን መብትለማስከበር ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የሰው ልጅ በሙሉ እኩልነትና ነጻነት ትልቅ አሻራ ጥለው አልፈዋል ሲሉ ተናገረዋል።

አሁን ላይ ያለው ትውልድም በውስጡ የተለያየ አመለካከት ቢኖረውም እንኳ ሀገሩን በተመለከተ እንደ ቀደሙት አባቶች በአንድነት እንዲቆም  ነው ያሳሰቡት።

ነገን የተሻለ ለማድረግና የሁላችን የሆነችውን ሀገር ለመገንባት በጋራ ተባብሮ በመስራት በኢኮኖሚ ማበልጸግ ይገባናልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ጥንታዊት ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፈን በበኩላቸው ኢትዮጵያ በጀግኖቿ በወራሪው ጣሊያን ላይ የተቀዳጀችው ድል የሰው ልጅ ሁሉ በእኩልነት እንዲታይ ያደረገ ድል መሆኑን ነው የተናገሩት።

እንደ ሀገር የሚያጋጥሙ ችግሮችን ተቀራርቦ በመነጋገር መፍታት እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

በዚህ በዓል ላይ የተገኙ አባቶችም ይህን በዓል ከማክበር ባለፈ ጀግኖች አባቶች ሀገሪቷን ከፍ ለማድረግ የከፈሉትን ዋጋ በማሰብ ጭምር ሊሆን ይግባልም ብለዋል።

የአሁኑ ወጣትም ይህን አባቶች የከፈሉትን ዋጋ በመረዳት ለአንድነት ሀገርን በኢኮኖሚ ለማሳደግ መሰረት መጣል ይገባቸዋል ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም