መንግስት የጤናውን ዘርፍ ችግሮች ለመፍታት ፖሊሲ እስከመቀየር ቁርጠኛ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

95

ሚያዝያ 26/2011 የጤናውን ዘርፍ ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል አሳማኝ የውሳኔ ሃሳብ ከቀረበ መንግሥት የዘርፉን ፖሊሲ ለመቀየር ዝግጁ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ከተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች ከመጡ ከ3 ሺህ በላይ ከሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ የጤና ባለሙያዎቹ ሥራ ላይ ያለው የጤና ፖሊሲ የተለያዩ ችግሮች እየተስተዋለበት መሆኑን ገልጸዋል።

ያም ብቻ ሳይሆን ፖሊሲው በሁሉም እርከን የሚገኙ የጤና ባለሙያዎችን ከግምት ያስገባ አለመሆኑን ነው ያስቀመጡት። ይህም በአሰራር ላይ ክፍተት መፍጠሩን በመጠቆም።

ለአብነትም የጤና ባለሙያዎች ከዩኒቨርስቲ ተመርቀው ከወጡ በኋላ ከመጠን በላይ የወጪ መጋራት ክፍያ እየተጠየቁ መሆኑን አንስተዋል።

ጀማሪ የጤና ባለሙያና በርካታ ዓመታትን በዘርፉ ልምድ ያለው ባለሙያ ከአሰራሩ ጋር በተያያዘ ተመሳሳይ ክፍያ እየተሰጣቸው እንደሆነም ጠቁመዋል።

የጤና ባለሙያዎች የአገልግሎት ጊዜያቸውን ከጨረሱ በኋላ እንደ ማንኛውም ግለሰብ ክፍያ ለምን ከፍለው ይታከማሉ የሚልም ኃሳብ አንስተዋል።

የትርፍ ሰዓት ክፍያን በተመለከተ መንግሥት ቀጥተኛ በጀት ሳይሆን በተዘዋዋሪ መመደቡ የጤና ክፍያው እየቀረባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎች የጤና አገልግሎት ሥራና የመምህርነት አገልግሎትም ከክፍያው ጋር የሚመጣን አለመሆኑንም ነው ባለሙያዎቹ ያነሱት።

በመንግሥትና በግል የጤና ተቋማት ላይ የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች ወጥ የሆነ አሰራር ባለመኖሩ በተለይም የመንግሥት የጤና ተቋሙ እየተጎዱ ከሆኑን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበኩላቸው በጤና ባለሙያዎቹ ለተነሱት አንዳንድ ጥያቄዎች ከዚህ ቀደም መንግሥት ምላሽ መስጠቱን ተናግረዋል።

ለአብነትም የወጪ መጋራትን በተመለከተ የጤና ባለሙያዎቹ መክፈል ከሚችሉበት አቅም ጋር ባገናዘበ መልኩ አዋጁ መሻሻሉን ገልጸዋል።

የጤና ባለሙያዎችን ነጻ ህክምና እንዲያገኙም የማኅበራዊ መድህን አገልግሎት አዋጅ እየተሻሻለ ስለሆነ ጥያቄው አብሮ እንደሚመለስ አረጋግጠውላቸዋል።

እኩል ክፍያና ተያያዥ የክፍያ ችግሮችም ታይተው ከዚህ ቀደም ውሳኔ እንደተላለፈባቸው አስረድተዋል።

የተቀረቱንም ችግሮች መንግሥት ትኩረት አድርጎ የዘርፉ ፖሊስም ጭምር በማሻሻል መፍትሄ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

ነግር ግን ችግሮቹን ለመፍታት ዝርዝር ጽሁፍ ቀርቦ መንግሥትን ሊያሳምን እንደሚገባም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።

የጤና ባለሙያው የሚሰራው ሥራ የዘርፉን ሥነ-ምግባር እንዲሁም ጥራትን በተላበሰ መልኩ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

በዘርፉ የሚከሰቱትንም የህክምና ጉድለቶች፣ የጤና ባለሙያዎች ደኅንነትና ተያያዥ ችግሮች ለመፍታት በጋራ መረባረብ ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም