ሁለተኛው አገር አቀፍ የሞዴል ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ኢግዚቢሽን ሊካሄድ ነው

69
አዲስ አበባ ሚያዝያ 22/2010 ሁለተኛው አገር አቀፍ የሞዴል ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ኢግዚቢሽንና ባዛር ከየፊታችን ረቡዕ እንደሚከፈት የፌዴራል የከተሞች ስራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ አስታወቀ። ኤጀንሲው የበጀት ዓመቱን ሁለተኛው ዙር አገር አቀፍ የሞዴል ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ኤግዚቢሽንና ባዛር እንዲሁም የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈፃፀም አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል። የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አሰፋ ፈረደ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ኢንተርፕራይዞችን ከተጠቃሚው በማገናኘት ዘላቂ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ያለመ ኤግዚቢሽንና ባዛር ከቀጣይ ረቡዕ ጀምሮ ለተከታታይ ሰባት ቀናት ይካሄዳል። ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ከ200 በላይ ሞዴል ኢንተርፕራይዞች በኤግዚቢሽኑ እንደሚሳተፉ ገልፀው፤ ከተሳታፊዎቹ ውስጥ 50 በመቶው ሴቶች፣ 3 በመቶው ደግሞ አካል ጉዳተኞች መሆናቸውን ተናግረዋል። ኤግዚቢሽኑን ከ16 ሺህ በላይ ሰዎች እንደሚጎበኙትና የ4 ነጥብ2 ሚሊዮን ብር ሽያጭ እንዲሁም የገበያ ትስስር ይፈጠራል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልፀዋል። በአንደኛው ዙር አገር አቀፍ ኤግዚቢሽን ያልተሳተፉ፣ ሰፊ የስራ እድል የፈጠሩ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ብቁና ተወዳዳሪ ምርቶችን የሚያመርቱ ኢንተርፕራይዞች ለኤግዚቢሽኑ እንደተመረጡም አብራርተዋል። ከሚያዝያ 24 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም የሚካሄደው ኤግዚቢሽን ግዮን ሆቴል ፊት ለፊት ባለው ክፍት ቦታ የሚካሄድ እንደሆነም ነው የተናገሩት። በመጀመሪያው ዙር የአገር አቀፍ ኤግዚቢሽንና ባዛር ከሰባት ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ 157 ኢንተርፕራይዞች የተሳተፉ ሲሆን፣ የ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የገበያ ትስስር ተፈጥሯል። በዚህም በጀት አመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ1 ሚሊዮን 200 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም