የምዕራብ ጉጂና ጌዲኦ ዞኖች ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው እየተመለሱ ነው

70

ሚያዚያ 26/2011 በምዕራብ ጉጂና በጌዴኦ ዞኖች ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለሱ ስራ መጀመሩ ተገለጸ።
ከሁለቱም ወገን ከ8 ሺህ 500 መቶ በላይ ዜጎችን ወደ ቀያቸው መመለሰ መቻሉን ታውቋል።በምዕራብ ጉጂ ዞን ቀርጫ ወረዳ ከተጠለሉ ተፈናቃዮች መካከል 6ሺህ 319 ቀደምው ወደ ሚኖሩባቸው ቀበሌዎች መመለሳቸውን የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ቡቃቶ ተናግረዋል።

በወረዳው ቀርጫ ከተማ ከተጠለሉት በተጨማሪ ከጌዴኦ ዞን ገደብ ወረዳ 1ሺሀ189 ተፈናቃዮች መመለሳቸውን ገልጸዋል።

“ተፈናቃዮች መደበኛ ኑሯቸውን ሲጀምሩ ለችግር እንዳይጋለጡ መሰረታዊ የሆኑ የማብሰያና የመመገቢያ ቁሳቁስ ብርድ ልብስ እንዲሁም እህልና ሌሎች አስፈላፈጊ እቃዎች ቀርበውላቸዋል” ብለዋል።

ወደ ቀያቸው የተመለሱት ተፈናቃዮች ጥቃትና ትንኮሳ እንዳይደርስባቸው የጸጥታ ሀይሎች በየቀበሌው ተቀናጅተው እየሰሩ መሆኑን አስታውቀዋል።

በየአካባቢው የሚገኘው ነዋሪ ህብረተሰቡ በነቂስ ወጥቶ ለተፈናቃዮች አቀባበል ከማድረግ አንስቶ በቡድን በመሆን ጊዜያዊ መጠለያ በመስራት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።

በቀጣይ ቀናትም ሌሎች ተፈናቃዮችን የመመለስ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና በወረዳው በአንድ ሳምንት ጊዜ ወስጥም ተፈናቃዮችን ሙሉ ለሙሉ ለማሰመለሰ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። 

በጌዴኦ ዞን የገደብ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አየለ ማሮ በበኩላቸው ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለሱ ተግባር ትናንት መጀመሩን ገልጸዋል።

በወረዳው የተጎዱ ቤቶችን ልየታ በማድረግ መለስተኛ ጉዳት የገጠማቸውን በማደስ ተፈናቃዮችን ለመቀበል የሚያስችል ዘግጅት መደረጉንም ጠቁመዋል።

ከ1 ሺህ በላይ ተፈናቃዮችን በሶስት ዙር ከምዕራብ ጉጂ ዞን ቀርጫ ወረዳ ወደ ጌዴኦ ዞን ገደብ ወረዳ መመለስ መቻሉን አስታውቀዋል።

በቀጣይ ቀናትም የጌዴኦ ዞን ነዋሪ የሆኑ 10 ሺህ የሚሆኑ ተፈናቃዮችን ለመመለስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ተመላሽ ተፈናቃዮች በበኩላቸው ወደ ቄያቸው መመለሳቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረው አስኪቋቋሙ ድረስ መንግስት በቀጣይ ደጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል አቶ አሰፋ ታደስ እንዳሉት ለአንድ አመት ያህል ከጌዴኦ ዞን ገደብ ወረዳ ተፈናቅለው በገርባ ከተማ ተጠልለው ቆይተዋል።

በዛሬው እለትም ወደ ቀያቸውና አብረውት ወደ ኖሩት ማህበረሰብ መመለስ መቻላቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋልመንግስት በቀጣይ እስኪቋቋሙ ድረስ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያቀርብላቸው ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን በተለይ ከሁለቱም ወገን በማፈናቀል በመግደል በመዝረፍ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ የነበሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም