ቦይንግ 737 አውሮፕላን ተሳፋሪዎችን እንደያዘ ወንዝ ውስጥ ገባ

65

ሚያዝያ 26/2011 ንብረትነቱ የአሜሪካ የሆነው ቦይንግ 737 አውሮፕላን ተንሸራቶ ፍሎሪዳ በሚገኘው ቅዱስ ዮሃንስ ወንዝ ውስጥ ገባ።

አውሮፕላኑ 143 ተሳፋሪዎችን ይዞ ከኩባ ጓንታናሞ ቤይ ወደ ወታደራዊ ከተማ ጃክሰንቫይል ሲጓዝ የነበረ ሲሆን በተሳፋሪዎች ላይ የከፋ ጉዳት አለመድረሱን ቢቢሲ ዘግቧል።

በአደጋው በትንሹ 20 ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት እንደደረሰ ተገልጿል።

አውሮፕላኑ መብረቅ የቀላቀለ ዝናብ እየዘነበ ሳለ በወንዙ ማእበል ላይ በከባድ ሁኔታ በማረፍ በቅዱስ ዮሃንስ ወንዝ አቅራቢያ መግባቱ ተነግሯል።

በአውሮፕላኑ ከተሳፈሩት ውስጥ ሼሪል ቦርማን ለሲኤንኤን አውሮፕላኑ ተንሸራቶ ወንዝ ውስጥ መግባቱን ገልጸዋል።

አውሮፕላኑ መሬት ነክቶ በተደጋጋሚ እንደነጠረ በማስታወስ ከፓይለቱ ቁጥጥር ውጭ ሆኖ እንደነበር ግምታቸውን ተናግረዋል።

"በውሃ ውስጥ ነበርን፣ የት እንደነበርን መናገር አንችልም፣ ወንዝ ውስጥ እንሁን ውቅያኖስ መናገር አንችልም" በማለት የነበረውን ሁኔታ አስታውሰዋል።

ቦይንግ 737 ማክስ 8 ማክስ አውሮፕላን ከወራት በፊት ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ 157 ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ በቢሾፍቱ አቅራቢያ መከስከሱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም