የተመራቂዎችን የሥራ አጥነት ችግር ለማቃለል የኢንዱስትሪ ና ዩኒቨርሲቲ ትስስርን ማጠናከር ይገባል-ምሁራን

200

ሚያዚያ 26/2011 በከፍተኛ ትምህርት ተቋት ተመራቂዎችን የሥራ አጥነት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የኢንዱስትሪና ዩኒቨርሲቲ ትስስርን ማጠናከር እንደሚገባ ምሁራን አመለከቱ፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎችን የሥራ አጥነት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የኢንዱስትሪ ዩኒቨርሲቲ ትስስርን ማጠናከር እንደሚገባ ምሁራን አመለከቱ፡፡

ስድስተኛው አገር አቀፍ የዩኒቨርሲቲዎች ምርምር ተቋማትና የኢንዱስትሪዎች ጉባዔ በኮምቦልቻ ከተማ ተካሂዷል፡፡

ምሁራኑ በጉባዔው ላይ ባቀረቧቸው ጥናታዊ ጽሁፎች እንዳመለከቱት የተመራቂዎችን የሥራ እጥነት ችግር ለመፍታት የኢንዱስትሪ ና ዩኒቨርሲቲ ትስስርን በተግባር ታግዞ ማጎልበት ያስፈልጋል፡፡

በኢትዮጵያና በዓለም የአዳዲስ ቴክኖሎዎች ተመራማሪና መምህር ፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ የኢንዱስትሪና ዩኒቨርሲቲ ትስስርን በተግባር ትምህርት ማስደገፍ ከተቻለ፤ ወጣቶቹ ሥራ ፈጣሪ ለመሆን ያስችላል ብለዋል

“የዩኒቨርሲቲዎችና የኢንዱስትሪዎች ትስስር ለሥራ ዕድል ፈጠራ ያለው እንድምታ” የሚል  ርዕስ ባቀረቡት በዚህ ጥናታዊ ጽሁፍ ዩኒቨርሲቲዎች ከኢንዱስትሪው ጋር ያላቸው ግንኙነት በጥናት ላይ ባለመመስረቱ ተማሪዎቹ ከምረቃ በኋላ ሥራ ለማግኘት እንደሚቸገሩ ተናግረዋል።

ተማሪዎች ከፍተኛ ሃብት ወጥቶባቸው ተምረው ለሥራ አጥነት ብሎም ለሱሰኝነት መጋለጣቸው በኢኮኖሚው ዕድገት ላይ ተጽዕኖ እንዳለውም  ምሁሩ አመልክተዋል፡፡

ሌላዉ ጥናት አቅራቢ አቶ ፋሲል ወልደገብርኤል በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲዎች የሚያፈሯቸው ተማሪዎች ብቃት ስለሌላቸው ሥራ ፈጣሪ ለመሆን እንዳልቻሉ ይናገራሉ።

ዩኒቨርሲቲዎች በተማሪዎችም ክህሎታቸዉን የሚያዳብሩበት በቂ ላቦራቶሪ፤የተግባር ትምህርትና ምዘና እንዲሁም በእውቀት የዳበሩ መምህራን ባለማግኘታቸው በቆይታቸው መመረቃቸውን እንጂ፤ ራዕያቸውን አይመለከቱም ይላሉ፡፡

የመመሪያቂያ ጥናታዊ ጽሁፋቸዉም ከሌሎች የተቀዱና ችግር ፈቺ ባለመሆናቸው የተመራቂዎችን ሥራ የመፍጠር አቅም ገድቦታል በማለትም ያስረዳሉ ፡፡

በመሆኑም ልምድ ያካበቱ ኢንዱስትሪዎች ተመራቂ ተማሪዎችን በተግባር በማሰልጠን የሙያው ባለቤት አድርጎ ማውጣት ይገባል ባይ ናቸው፡፡

የአሜሪካና የአዉሮፓ አገራት ዩንቨርሲቲዎችና ኢንዱስትሪዎችን በማስተሳሰር ተመጋጋቢ በማድረጋቸዉ የሥራ አጥነትን ችግር ከመፍታታቸውም ባለፈ በኢኮኖሚው ተወዳዳሪ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በበኩላቸዉ ምሁራን የሚያቀርቧቸዉን ጥናታዊ ጽሁፎች ወደ ተግባር በመቀየር የሥራ አጥነትን ቁጥር ለመቀነስ እየተሰራ ነው፡፡

ለዚህም ይረዳ ዘንድ 45 ዩኒቨርሲቲዎች ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተጠሪ እንዲሆኑ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በየዓመቱ የሚካሄደዉ አገር አቀፍ የዩኒቨርሲቲዎችና ኢንዱስትሪዎች ትስስር ጉባዔም ተጨባጭ ለውጥ ማሳየቱን ጠቁመው፤ የላቀ ብቃት ያላቸውን ተማሪዎችን ተመርጠው የተሻለ ስልጠና እንዲያገኙ በመደረግ ላይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ተማሪዎች በየአቅራቢያቸው በሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የተግባር ትምህርት በማግኘትና ከሠራተኞች ጋር የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ይህም በኢንዱስትሪዉ የሚያጋጥመዉን የሰው ኃይል እጥረትን ከማቃለሉም በላይ ተማሪዎች ከተመረቁ በኋላ ሥራ አጥ እንዳይሆኑ ያደርጋል ብለዋል፡፡

ሚኒስቴሩ የውጭ ተሞክሮዎችን በመቀመር ቴክኖሎጂውን በማነቃቃት ኢኮኖሚውን ለማሳደግም ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ100 ሺህ በላይ ተማሪዎች እንደሚመረቁ በዚህ ወቅት ተገልጿል፡፡

በጉባዔው ከሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ከ300 በላይ ምሁራንና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።10 ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ዉይይት ይደረግባቸዋል፡፡