የአርጎባ ቋንቋን ለማበልጸግ እየሰራሁ ነው…የወሎ ዩኒቨርሲቲ

90

ሚያዚያ 26/2011  የአርጎባን ቋንቋ ከጥፋት ለመታደግ በምርምር የታገዘ ተጨባጭ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የወሎ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡

ቋንቋውን ከተጋረጠበት የመጥፋት አደጋ ለመታደግ ከብሄረሰቡ ተወላጆች፤ምሁራንና ባለድርሻ አካላት ጋር በኮምልቻ ከተማ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነ-ጹህፍ ትምህርት ክፍል ዲን ዶክተር እንድሪስ አባይ እንደገለጹት እስከ 16ኛዉ ክፍለ ዘመን መጨረሻ የአርጎብኛ ቋንቋ በምስራቅ ኢትዮጵያ ከላስታ እስከ ሐረር፣ በደቡብ ክፍል ደግሞ እስከ ደዋሮና ኮንሶ ድረስ ይነገር ነበር።

በዚህ ወቅት ከአጎራባችና አረብ ሀገራት ጭምር ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን አነቃቅቶ እንደነበረም ገልፀዋል፡፡

“ይሁን እንጂ ትኩረት በማጣቱ ቀስ በቀስ ቋንቋው በአማረኛ፣ በአፋረኛ፣ በኦሮምኛና በሌሎች ቋንቋዎች እየተተካ የመጥፋት አደጋ ተጋርጦበታል”ብለዋል፡፡

“ቋንቋውን ከጥፋት ለመታደግም ወሎ ዩኒቨርሲቲ ጥናቶችን በማድረግና ህብረተሰቡን በማወያየት ቋንቋው እንዲስፋፋ የሚያግዙ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል”ብለዋል፡፡

ለዚህም ካለፈው ዓመት ጀምሮ መዝገበ ቃላት፣ የጎልማሶችና ከአንደኛ እስከ አራት ክፍል መምሪያ መጽሐፎች ታትመው እንደ አንድ የትምህርት አይነት እንዲሰጥ ለማድረግ ሙከራ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በከሚሴ መምህራን ኮሌጅም አንደ አንድ የትምህርት አይነት መሰጠት መጀመሩን የተናገሩት ዶክተር እንድሪስ በቅርቡም በዩኒቨርሲቲውም ተሞክሮው ይጀመራል ብለዋል።

በመድረኩ "የአርጎብኛ ቋንቋ ከየት ወዴት" የሚል ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት አቶ ይማም መሃመድ በበኩላቸው በምስራቅ ኢትዮጵያ በርካታ ተናጋሪዎች ቢኖሩትም ከ50 ዓመት በፊት ጀምሮ እየተዳከመ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

ለዚህም በስርዓተ ትምህርቱ ተቀርጾ አለመሰጠቱ፣ የሚነገርበት አካባቢ የስራ ቋንቋ ሌላ መሆኑ፣ ቋንቋውን ጠንቅቀው የሚያውቁ አባቶች ወደ ሌላ ቦታ መሰደድ፣ በትኩረት ማነስ እንደ አማራጭነት መጠቀሚያ መሆኑና ሌሎችም ምክንያት መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

“ቋንቋው ‘ሾንኬ ጠለሃ’ እና ‘አልዩ አምባ’ በሚባሉ ሁለት ዘዬዎች የሚነገር ሲሆን ከወረዳው ባለፈ በአፋር፣ በኦሮሞ ብሄረሰብና በሰሜን ሽዋ ዞን ቢነገርም በየአካባቢው ቋንቋ በመተካቱ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል”ብለዋል፡፡

በጥናታቸዉም በአርጎባ ብሄረሰብ ልዩ ወረዳ ቋንቋውን ከሚሞክሩ 40 ሺህ ዜጎች መካከል የሚያነቡ፣ የሚጽፉና ዘዬውን ጠንቅቀው የሚያውቁ ከአንድ ሺህ እንደማይበልጡ ጠቅሰው፤ እነዚህም ቢሆን እድሜያቸው የገፋ መሆኑን እንደ ስጋት አንስተዋል፡፡

የአርጎባ ብሄረሰብ ልዩ ወረዳ ነዋሪ አቶ አህመድ ኑሩ ቋንቋውን በማስተማር ለትውልዱ ለማስተላለፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

የአካባቢውን ህብረተሰብና ወጣቱን እያስተማሩ ከመሆናቸውም ባለፈ ቀላል መዝገበ ቃላት፣ አርጎበኛ ቋንቋ ለጀማሪዎች የሚሉ መጽህፎችን ማሳተማቸውን ተናግረዋል፡፡

በሙከራ ላይ ላለው ከአንደኛ እስከ 4ኛ ክፍል መማሪያ መጽሐፍም ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

“ቋንቋው የኔ የሚል ተቆርቋሪ አጥቶ እንጅ በየገጠሩ መጻፍና ማንበብ ባይችሉም በርካቶች ይናገሩታል” ብለዋል፡፡

ቀጣይ ከአጋር አካላት ጋር ተረዳድተው የወረዳው የሥራ ቋንቋ ለማድረግም እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ሌላዋ ወይዘሮ ፈጡማ አህመድ በከሚሴ መምህራን ኮሌጅ በ2011 ዓ.ም ከአንደኛ እስከ 4ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችን የሚያስተምሩ 32 ተማሪዎችን እያሰለጠኑ መሆናቸውንና ቋንቋው እንዲሰፋፋ የእናትነት ድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡

ቋንቋዉን የሚናገሩ ዜጎች ለጎረቤቶቻቸውና ለልጆቻቸው እንዲያስተምሩ ጠይቀዋል፡፡

“የአርጎበኛ ቋንቋ በጉራማይሌ ደረጃም ቢሆን በአፋር፣ በኦሮሞ ብሄረሰብ፣ በሰሜን ሸዋና ደቡብ ወሎ ዞን አካባቢ አሁንም ይነገራል” ብለዋል፡፡

የወሎ ዩኒቨርሲቲ የአርጎበኛ ቋንቋን ጨምሮ በወሎ አካባቢ የሚነገሩ አፋርኛ፣ ትግርኛ፣ ኦሮሞኛና አረብኛ ቋንቋዎችን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ለሁለት ቀናት በተካሔደው ውይይት ላይ አራት ጥናታዊ ፅሁፎች የቀረቡ ሲሆን የብሄረሰቡ ተወላጆች፣ ምሁራንና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም