የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ብቁ የፖለቲካ ምሁራንን ለማፍራት በትኩረት እንዲሰሩ ተጠየቀ

216

አዲስ አበባ ሚያዚያ 25/2011በየቀኑ የሚቀያየረውን የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ትኩሳት ቀድመው ተረድተው መፍትሄ የሚያስቀምጡ የፖለቲካ ምሁራንን ማፍራት ላይ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ትኩረት ሰጥተው በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ።

“የፖለቲካ ሁኔታ ተለዋዋጭነት በአፍሪካ ቀንድና የሰላም ጅማሮዎችን ማስቀጠል” በሚል መሪ ሃሳብ ቅድመ ጣና ፎረም በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከተለያዩ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ምሁራን መክረዋል።

በውይይቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የግብጽ ሳዳት ሲቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር አህመድ ባዮሚ እንደገለጹት በየጊዜው የሚያገረሸው የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ትኩሳት ዋነኛው ምክንያት በብቁ የፖለቲካ አመራሮች ስለማይመሩ ነው።

የአፍሪካ ሀገራት በተለይም የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የፖለቲካ አመራሮች ለሚመሩት ሀገር የማይመጥንና የምዕራብአዊያንን የፖለቲካ ፍልስፍና የተካኑ መሆናቸው ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ተናግረዋል።

ለአፍሪካ የሚያስፈልጋት የራሷን ችግር የሚረዳ ነባራዊ ሁኔታውን ከግምት ውስጥ ያስገባ የፖለቲካ ትምህርት የተማረ አመራር እንደሆነም ተናግረዋል።

“ነገር ግን ይህ ባለመሆኑ፣ ለቀጣይ በአፍሪካ ቀንድ በየቀኑ የሚያገረሸውን የፖለቲካ ትኩሳት ለማረጋጋትና ለችግሩ መፍትሄ ለማግኘት የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ለአህጉሪቱ ችግር የሚመጥን ስርአተ ትምህርት ቀርጸው ብቁ አመራሮችን ሊያወጡ ይገባል”ብለዋል።

እንደ “ኢጋድ” ያሉ ለአፍሪካ ቀንድ ችግርን ይፈታሉ ተብለው የተቋቋሙ ተቋማትም ሳይቀር በሰው ሃይል የአቅም ውስንነት ምክንያት ተገቢውን ስራ እያከናወኑ አንዳልሆነ አስረድተው፤ ለዚህም አፍሪካዊያን አንድ መሆንና የትምህርት ስርአታቸውንም በራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ሊቀርጹ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በቀጠናው አገራት መካከል በአንዱ ላይ ችግር ከተፈጠረ ለሌሎችም እንደሚተርፍ ያስረዱት የደቡብ ሱዳን ጁባ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ጆን አፑሮት “የሚፈጠሩ ችግሮች የጋራ ስለሆኑ በጋራ መፍትሄ ሊፈለግ ይገባል”ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ ትምህርት ላይ ትኩረት በመስጠት የተማረ የሰው ሃይል መጠንን ማሳደግና የትምህርት ጥራትንም በዛው ልክ መቃኘት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።

ከአመታት በፊት በሶማሊያ የተፈጠረው አለመረጋጋት በአሁኑ ሰአት አብዛኛውን የአፍሪካ ቀንድ እያዳረሰ እንደሆነም አመልክተዋል።

“ስለሆነም የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የአህጉሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ያስገባ ጥናትና ምርምር በማድረግ በዛ የተቃኘ የፖለቲካ ልሂቃንን ማፍራት የጠበቅባቸዋል”ብለዋል።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ችግሩን በመገንዘብ ከተለያዩ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ያስረዱት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኝ ናቸው።

ሁሉም የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የአፍሪካ ፖለቲካ የተረጋጋ በሚሆንበት ጉዳይ ላይ በጋራ ተባብረው ሊሰሩ እንደሚገባም አስታውቀዋል።

“የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከ300 በላይ የአፍሪካ ተማሪዎችን በስኮላር ሺፕ የትምህርት እድል እየሰጠ መሆኑን ተናግረው ሌሎች የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎችም ሊተገብሩት ይገባል” ሲሉ ገልፀዋል።

በዚሁ የጣና ፎረም ቅድመ ውይይት ላይም ከተለያዩ የአፍሪካ ዩኒቨርስቲዎች የተውጣጡ ምሁራንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ዙሪያ የሚመክረው 8ኛው የጣና ፎርም የተለያዩ ሃገራት መሪዎችና ምሁራን በተኙበት በነገው እለት ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።