የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዚደንት በልማት ዙሪያ ከምዕራብ ሐረርጌ ዞን ነዋሪዎች ጋር ተወያዩ

82

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዚደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በፖለቲካና ልማት ዙሪያ ዛሬ በጭሮ ከተማ ከምዕራብ ሐረረጌ ዞን ከተወጣጡ ነዋሪዎች ጋር ተወያዩ። 

በስፍራው የተገኙት ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በአካባቢው የመሰናዶ ትምህርት ቤት ለመገንባት  የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።

በውይይቱ  ወቅት ነዋሪዎቹ እንዳሉት የተገኘውን ሀገራዊ ለውጥ ከዳር ለማድረስ የኦሮሞ ህዝብና መንግሰት የሚያደርጉትን ጥረት በመደገፍ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ ናቸው።

አቶ ሰላዲን ሀሽም የተባሉት ነዋሪ በሰጡት አስተያየት በአካባቢያቸው የተለያዩ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዳላገኙ ተናግረዋል።

የተጀመሩ የተለያዩ ፕሮጀክቶችም ከዳር ሳይደርሱ እንደሚቆሙ የገለጹት አስተያየት ሰጪው መንግሰት ትኩረት ሰጥቶት እንዲያስፈጽም ጠይቀዋል።

" በአከባቢያቸው ከሚገኙ ወንድም የሶማሌ  ብሄር ተወላጆች ጋርም በሰላም እየኖርን እንገኛለን፤ ወደፊትም እናሰቀጥላል "ብለዋል።

የጭሮ ከተማ ነዋሪው ወጣት ሱሌማን ከዲር በበኩሉ  መንግሰት ለዞኑ ህብረተሰብ በቂ ትኩረት እንዳልሰጠና በአካባቢው ለተነሱ የተለያዩ የልማት ጥያቄዎች  ምላሽ እንዳላገኙ ተናግሯል።

በተለይ የውሀ ፣ የኤሌክትሪክ  መብራት እና የመንገድ መሰረተ ልማት እንዲሁም ለወጣቱ የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ መንግስት  ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቋል። 

የክልሉ ምክትል ፕሬዚደንት  አቶ ሽመልስ አብዲሳ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ምዕራብ ሐረርጌ በርካታ  ኢትዮጵያዊያን ብሔር ብሔረሰቦች በፍቅርና በአንድነት የሚኖሩበትና  ለነጻነት የተሰው ጀግኖችን ያፈራ አካባቢ ነው።

ይህንን ደማቅ ታሪክ ወጣቱ ትውልድ ማስቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

አቶ ሽመልስ  "በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ  ፈጣን ለውጥ ውስጥ መሆኗን በመረዳት ከሌሎች የሀገሪቱ  ህዝቦች ጋር በመሆን  የተጀመረውን ለውጥ ከዳር ማድረስ ይኖርብናል" ብለዋል።.

ነዋሪዎቹ ላነሷቸው  የልማት ጥያቄዎችና በጅምር ለቀሩ ፕሮጀክቶች ደረጃ በደረጃ ምላሽ ለመስጠት   መንግስት  እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

ከውይይቱ በኋላ ምክትል ፕሬዝደንቱና  ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው  በምዕራብ ሐረርጌ  ሀዊ ጉዲና ወረዳ ቢልቃ ቀበሌ በቀደምት ሴት ታጋይ "ቱጂ ባሬንቶ  " የተሰየመ የመሰናዶ ትምህርት ቤት ለመገንባት  የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም