በልባዊ ይቅርታ ሰላማችንንና አንድነታችንን እናጠናክራለን---የአማራና ቅማንት የሰላም ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች

69

ሚያዝያ 25/2011 እርቁን ከልባቸው በመያዝ በሰነ-ልቦናና በንብረት ላይ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖችን ከጎናቸው ሆነው እንደሚደግፉ የቅማንትና የአማራ ህዝቦች እርቀ ሰላም ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች ተናገሩ፡፡

በእርቀ ሰላሙ በሁለቱ ህዝቦች መካከል የነበረውን አንድነትና ፍቅር መመለስ አማራጭ የሌለው የጋራ ስራ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

ከተሳታፊዎች መካከል ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን ነባሩ ጭልጋ ወረዳ የመጡት አቶ ጎሸ አባይ እንደተናገሩት በአካባቢው በነበረው ግጭት በሰዎች ህይወትና ንብረት መጥፋት አዝነዋል

ይሁን እንጂ በተሳሳተ መንገድ የተፈፀመውንና ያለፈን ይቅር በማለት ነባር ፍቅራቸውን በፅኑ መሰረት ላይ መገንባት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡

“ከቀያቸው ተፈናቅለው የነበሩ ወገኖች ወደ ነበሩበት ሲመለሱ መንግስት ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ ሁላችንም የአቅማችንን እገዛ እናደርጋለን” ብለዋል፡፡

“አንዳንድ የሃይማኖት አባቶች ሀይማኖታዊ ተልዕኳቸውን አልተወጡም ነበር” ያሉት አቶ ጎሸ “በዚህ እርቅ ላይ ከሁለቱም ወገን ለማፈንገጥ የሚሞክርን ግለሰብ ማውገዝ ይኖርባቸዋል” ብለዋል፡፡

ከምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ የመጡት አቶ ገብሬ ከበደ በበኩላቸው ባለፉት ወራት በደረሰው የወገን ሞትና ጉዳት በመፀፀት ዳግም ወደ ግጭት በማይገቡበትና ነባር አንድነታቸውን በሚመልሱበት ሁኔታ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

የግጭቱ ሰለባ የሆኑ ወገኖችን በጉልበትና በቁስቁስ በመደገፍ አሁን ካሉበት ተረጂነት እንዲወጡና ተመልሰው ሀብትና ንብረት እንዲያፈሩ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል፡፡

በዚህ እርቀ ሰላም ኮንፈረንስ ላልተገኙ የአካባቢው ነዋሪዎች ግንዛቤ በመፍጠር የተፈናቀሉ ወገኖችን በይቅርታና በፍቅር እንደሚቀበሉም ነው ያስረዱት፡፡

“ተጠያቂነትን በመዘርጋት ህግ እንዲከበር ለማድረግ የእኔ ብሔር ከሚል አስተሳሰብ ወጥተን እርቁ የመጨረሻ እንዲሆን እንሰራለን” ያሉት ደግሞ ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን ላይ አርማጭሆ ወረዳ የመጡት አቶ በለጠ ኖራሁን ናቸው፡፡

በመሆኑም ህዝቡ የህገወጦች መደበቂያ ምሽግ ከመሆን መውጣትና ሁሉም በጥፋቱ ልክ በህግ ተጠያቂ እንዲሆን የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

የኢፌዴሪ ሀገር መከላከያ ሠራዊት የኢንዶክትሬሽን ኃላፊ የሆኑት ሜጀር ጀኔራል ሙሃመድ ተሰማ በበኩላቸው ይህ የእርቀ ሰላም ኮንፈረንስ አካባቢውን ወደ ነበረበት ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንደሚመልሰው እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ግጭቱ በአካባቢው ህብረተሰብ ላይ ምን ያክል የስነ ልቦና ተፅዕኖ አሳድሮ እንደነበርና ህዝቡ ለሰላሙ ያለውን ከፍተኛ ፍላጎት ያዩበት መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

“ያለፉ ቁስሎችን በመርሳት በሚያክሙ ሥራዎች ላይ መሳተፍ አለብን፤ መከላከያ ሠላም እንዲረጋገጥ እና እርቁ እንዲሰምር እስከ መንደር ድረስ በሚካሄደው ምክክርድጋፍ ያደርጋል”ብለዋል፡፡

በሰላም ሚኒሰቴር የአቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አምባየ ወልዴ በአንፃሩ እርቀ ሠላሙ የፀና እንዲሆን የተፈፀመውን በደል ማመን እና ኃላፊነት መውሰድ፣ መፀፀትና ይቅርታ መጠየቅ ከልብም ይቅር ማለት ይጠበቃል ብለዋል።

“ፍቅርንና ሰላምን የሚተካ የለም” ያሉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ይቅርታን ተቀብለው የፀና እርቅ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

ህግን በማስከበር በኩል መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን ጠቅሰው ህዝቡ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግም አሳስብዋል፡፡

የእርቀ ሰላም ኮንፈረንሱ በሀይማኖት አባቶች አስፈፃሚነት በጸሎትና በይቅርታ ዛሬ ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም