የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ነዋሪዎች የመሠረተ ልማት ተቋማት እንዲገቡላቸው ጠየቁ

82

ሐረር ሚያዝያ  25/ 2011 የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ነዋሪዎች የመሠረተ ልማት ተቋማት ግንባታ ጥያቄዎቻቸው እንዲመለሏቸው ጠየቁ።

ነዋሪዎቹ ከኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ጋር በሐረር ከተማ ተወያይተዋል።

ነዋሪዎቹ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት  የመንገድ፣የጤና ተቋማትና የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግሮቻቸውን የሚፈቱ ፕሮጀከቶች ሊገነቡላቸው ይገባል።

የልማት ጥያቄዎቻቸውን ላለፉት ዓመታት ሲያቀርቡ  እንደነበረም ለምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውሰዋቸዋል።

የግራዋ ወረዳ ነዋሪ አቶ አብዱላዚዝ መሐመድ እንደተናገረው ወረዳውን ከአዴሌ የሚያገናኝ እስፋልት መንገድ ለመስራት የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠ አንድ  ዓመት እንዳለፈው ተናግረዋል።

መንገዱ ባለመገንባቱም ምርታቸውን  ለገበያ ለማቅረብ  እንዳልቻሉና በተለይም ከቁም እንስሳት ገበያ ተጠቃሚ ባለመሆናቸው መፍትሄ እንዲፈልግላቸው ጠይቀዋል።

የሆስፒታልና የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግሮቻቸውን ለመፍታት ግንባታቸው እየተካሄዱ ያሉት ፕሮጀከቶች መጓተታቸውን የሚገልጹት ደግሞ የጉርሱም ወረዳ ነዋሪ አቶ በክሪ አብዱከቡር ናቸው።

አባ ገዳ ሙሳ ሮባ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው ለመጠጥና ለመስኖ የሚያገለግል ውሃ ለማግኘት 40 ሜትር ወደ ታች ጥልቅ ጉድጓድ መቆፈር እየጠየቃቸው በመሆኑ በዘርፉ የተያዙ ፕሮጀክቶችን በማከናወን አስቸኳይ መፍትሄሊ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

 የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በነዋሪዎቹ የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ የጋራ ጥረት ማድረግ እንደሚያሰፈልግ  ተናግረዋል።

በተለይ የተጀመሩና የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠባቸውን የመንገድና ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ  እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

በከተማው ጨለንቆ ሰማዕታት አዳራሽ በተካሄደው ውይይት የክልሉና በየደረጃው የሚገኙ  አመራሮችና የነዋሪዎች  ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም