ለህዝብ ተጠቃሚነት በጋራ እንሰራለን---የኦሮሚያ፣የሶማሌና የሀረሪ ክልሎች ርዕሳነ-መስተዳድሮች

72

ሚያዝያ 24 / 2011 ያለ አንዳች የጸጥታ ችግር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎችን በትኩረት እንሰራለን ሲሉ የኦሮሚያ የሶማሌና የሃረሪ ክልሎች ርዕሳነ-መስተዳድሮች ገለጹ።

ያለ አንዳች የጸጥታ ችግር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎችን በትኩረት እንሰራለን ሲሉ የኦሮሚያ የሶማሌና የሃረሪ ክልሎች ርዕሳነ-መስተዳድሮች ገለጹ።

በምስራቅ ሀረርጌ ዞን ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ነዋሪዎች ጋር በሃረር ከተማ ውይይት ተደርጓል።

በመድረኩ ላይ የኦሮሚያ የሀረሪና የሶማሌ ክልሎች ርዕሳነ-መስተዳድሮች እንደተናገሩት የህዝቡን ጥያቄ የሚመልሱና ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎችን በጋራ ለማከናወን ተስማምተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት ግጭቶችን በማስወገድ የህዝብን ጥቅም ለማስቀደም በጋራ መስራት አስፈላጊ ነው።

በዚህም መሰረትም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ በጋራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳደር ሙስተፌ ኡመር በበኩላቸው በህዝቦች መካከል የነበሩ የተሳሳቱ ተግባራትን በመታገልና በማስቀረት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ክልላቸው በትኩረት ይሰራል።

የኦሮሚያ ክልል ልማት የሶማሌ ክልል ልማት መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ርዕሰ-መስተዳደሩ “በተለይ በአካባቢው የተዘጉ የንግድ እንቅስቃሴዎች በአፋጣኝ ይጀምራሉ”ብለዋል።

“በዛሬው እለት ከአዳማ እስከ ሀረር ስጓዝ በዞኑ የተመለከትኩት የልማት ስራ ያሰብኩትን ያክል ባለመሆኑ በዚህ ላይ ህብረተሰቡ በትኩረት ሊሰራበት ይገባል” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

“ወቅቱ ያለፈውን ታሪክ በመተው ሌላ ተጨማሪ ታሪክ ለመስራት የምንሰረራበት ነው” ያሉት የሃረሪ ክልል ርዕሰ-መስተዳደር አቶ ኦርዲን በድሪ “የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን በማጠናከር በጋራ መስራት ይጠበቅብናል”ብለዋል።

“ክልሉ ከአጎራባች ክልሎች ጋር የጀመረው የሰላም የልማትና ሌሎች ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ”ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም