ህዝቡ በሰከነ መንገድ ችግሮቹን ለመፍታት መስራት አለበት---ዶክተር አምባቸው

89

ሚያዝያ 24/2011ህዝቡ በተለመደው ጨዋነትና የመከባበር ባህል በመተሳሰብ የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍታት እንዳለበት የአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳደር አስታወቁ።

የጎንደር ከተማን ጨምሮ ከሰሜን፣ ከማእከላዊና ከምእራብ ጎንደር ዞኖች የተውጣጡ የህዝብ ወኪሎች ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር የህዝብ ምክክር መድረክ ዛሬ በጎንደር ከተማ ተካሂዷል።

ርእሰ መስተዳድሩ ዶክተር አምባቸው መኮንን በመድረኩ እንደተናገሩት አዲሱ የክልሉ አመራር ለህግ የበላይነትና ለሰላም መረጋገጥ ከህዝቡ ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ ይገኛል።

በክልሉ ለውጡን ተከትሎ እየታዩ ያሉትን የሰላም እጦት አለመረጋጋትና ግጭቶች በመፍታት በኩል አመራሩ የጀመረውን ጥረት በማገዝ የህዝቡ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ህዝቡ ወደ ጥንቱ የጨዋነት ባህሉና መተሳሳብ ብሎም ወደ መከባበርና መቻቻል መመለስ ብለዋል፡፡

“ማስተዋል በእጅጉ የሚጠይቅበት ወቅት ላይ ነው ያለነው፤ በስሜት የምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሌላ ችግር እየፈጠሩብን እያየን በመሆኑ ከዚህ ችግር ፈጥኖ መውጣት ግድ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

“ከምንግዜውም በላይ በመንግስትና በህዝብ፤ በመሪ ፓርቲና በህዝብ መካከል ተቀራርቦና ተመካክሮ ተግባብቶና የጋራ አቅጣጫ ተልሞ የጋራ መፍትሄ መፈለግ ተገቢና ወቅታዊ ነው” ብለዋል፡፡

ሰላም ዋጋው የትየሌለ ነው፤ ሰላም ከሌለ ልማት እድገትና ብልጽግና የሚባል ነገር አይታሰብም ስለሆነም የጎንደር ህዝብ ሰላሙን ለማረጋገጥ የጀመረውን ትግል ዛሬም እንደትናንቱ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባልም ብለዋል።

“ዜጎች በቀያቸው ተረጋግተው እንዲኖሩ የህግ የበላይነትን በማስከበር መንግስት ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ይሰራል” ሲሉም ተናግረዋል።

የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ሙሉቀን አዳነ በበኩላቸው የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ወደ ከተማው መምጣት የከተማውንና አካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከህዝቡ ጋር መምከራቸው መልካም አጋጣሙ ነው።

በሀገሪቱ በተጀመረው ለውጥ በርካታ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ መሻሻሎች መታየት መጀመራቸውን ጠቅሰው፤የከተማው ህዝብ የለውጡን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ለሰላሙ ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲንቀሳቀስ ጠይቀዋል።

የጎንደር ከተማ የሰላምና የልማት ሸንጎ ሰብሳቢ አቶ ባዬህ በዛብህ በበኩላቸው እንደገለጹት ሸንጎው ለከተማውና ለአካባቢው ሰላም መረጋገጥ ህዝቡን በማስተባበር እየሰራ ነው፡፡

የክልሉ ከፍተኛ አመራር በከተማው የሚታዩ የመልካም አስተዳደር፤ የስራ እጥነት፤ የህገ-ወጥ ንግድና የህገ-ወጥ ቤቶ ግንባታ መስፋፋት እንዲሁም የህዝቡን አንገብጋቢ የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ አሳስበዋል፡፡

የምክክር መድረኩ ተሳታፊ ወጣት የሽዋስ አዲስ በበኩሉ “ዛሬ በመላ ሀገሪቱ ለተቀጣጠለው ህዝባዊ ለውጥ የጎንደር ከተማ ወጣቶች ግንባር ቀደም መስዋእትነት ከፍለዋል” ብሏል፡፡

የከተማው ወጣቶች በስራ እጦት ለኢኮኖሚዊና ማህበራዊ ችግሮች ተጋላጭ እንደሆነ ጠቁሞ የክልሉ መንግስት ለከተማው ፍትሃዊ በጀት በመመደብ ወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጥር ጠይቋል።

ለግማሽ ቀን በቆየው ህዝባዊ የምክር መድረክ የክልሉና የዞኖቹ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የሃይማኖት አባቶች የሀገር ሽማግሌዎች ወጣቶችና ሴቶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም