ግዙፉ የመስኖ ፕሮጀክት ያለ አገልግሎት 33 ዓመታትን አስቆጠረ

86

ሚያዝያ24/2011 በምስራቅ ሸዋ ዞን 3ሺህ ሔክታር መሬት እንዲያለማ ከ33 ዓመታት በፊት በ45 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ዘመናዊ የመስኖ ፕሮጀክት ከ200 ሔክታር መሬት በላይ ሳያለማ መቆየቱ እንዳሳዘናቸው ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለፁ ።

የመስኖ ልማት ፕሮጀክቱ 3ሺህ ሔክታር መሬት እንዲያለማ ተብሎ ዘጠኝ ትላልቅ ማሽኖች ቢገጠሙለትም እስካሁን የሚሰራው አንዱ ብቻ መሆኑም አነጋጋሪ ሆኗል።

አቶ ቱራ ሁሴን የመቂ መስኖ ልማት ፕሮጀክቱ በምስራቅ ሸዋ ዞን ዱግዳ ወረዳ በቀሌ ግሪሳ በተባለው ቀበሌ በ1978 ዓም ሲዘረጋ በቦታው የነበሩና የፕሮጀክቱ የፓምፕ ሰራተኛ ሆነው ላለፉት 23 ዓመታት አገልግለዋል።

ፕሮጀክቱ በወቅቱ በነበረው ጥሩ  የገንዘብ የመግዛት አቅም በ45 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ ቢሆንም እስካሁን መስራት ያለበትን ያክል ባለመስራቱ ይቆጫሉ።

ሶስት ሺህ ሔክታር መሬት የሚያለማ ውሃ እንዲያወጡ የተገጠሙት ዘጠኝ ትላልቅ መሳሪያዎች በጋራ ተቀናጅተው ሲሰሩ የተመለከቱት በሙከራ ውቅት ብቻ እንደነበረም አቶ ቱራ  ይናገራሉ ።

ከዚያ በኋላ ግን ከሶስት በላይ ማሽኖች አገልግሎት ሲሰጡ እንዳልተመለከቱና ብልሽት ከሚል ሰበብ ውጪ ምክንያቱን እንደማያውቁ በመግለፅ የአካባቢው አርሶ አደሮች ብቻ ሳይሆን ሀገር የሚጠቅም ፕሮጀክት አለአግባብ መባከኑ እንደሚያሳዝናቸው ገልፀዋል ።

እንዲያውም ላለፉት አራት ዓመታት በስራ ላይ ያለው አንድ ማሽን ብቻ መሆኑን ተናረዋል ።

አቶ ወልዴ ብርመጂ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ በሰጡት አስተያየት “ፕሮጀክቱ በብልሽት ምክንያት አገልግሎት አይሰጥም ተብሎ በርካታ ሰዎች እየተመላለሱ ቢያመለክትም መፍትሔ ይዘው ወደ ስራ ሲገቡ አላየሁም” ብለዋል ።

ሀገር የሚጠቅም ግዙፍ ተቋም በመሆኑ የፌዴራልና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በቅርበት ተመልክተው መፍትሄ እንዲሰጡበትም አስተያየት ሰጪው ተናግረዋል ።

በዱግዳ ወረዳ ግብርና ልማት ፅህፈት ቤት የጥቃቅን መስኖ ልማት ባለሙያ አቶ ምትኩ ነጋሽ እንደገለፁት ፕሮጀክቱ የአካባቢውን አርሶ አደሮች የኑሮ ሁኔታ ይለውጣል ተብሎ ከ33 ዓመታት በፊት በኮሪያ ባለሙያዎች የተዘረጋ ነው ።

ሦስት ሺህ ሔክታር መሬት በማልማት በአካባቢው የሚኖሩ 773 አባወራ አርሶ አደሮችን ወደ ላቀ የኑሮ ደረጃ ለማሸጋገር ታስቦ የተዘረጋ ቢሆንም ከ9ኙ ትላልቅ ማሽኖች አንዱን ብቻ በማንቀሳቀስ ማልማት የተቻለው 225 ሔክታር መሬት ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

“የመስኖ ልማት ፕሮጀክቱ በሙሉ አቅሙ መስራት ያልቻለው በብልሽት ምክንያትና መለዋወጫ ዕቃው እንደልብ በቅርብ ማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ ነው” ብለዋል።

አሁን ግን ሶስቱን ማሽኖች ብቻ እንኳን በማንቀሳቀስ 450 ሔክታር መሬት ማልማት እንደሚቻል በጥናት በመረጋገጡ ከኦሮሚያ በጀት ተመድቦለት ለማንቀሳቀስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ባለሙያው ተናግረዋል ። 

የዱግዳ ወረዳ አስተዳደር የህዝብ ቅሬታ ሰሚ የስራ ሒደት ባለቤት አቶ ባቲ አቡ የአካባቢው አርሶ አደሮች ፕሮጀክቱ የተሟላ አገልግሎት ባለመስጠቱ ምክንያት በተደጋጋሚ ቅሬታ ማሰማታቸውን ገልፀው ከወረዳው አቅም በላይ በመሆኑ ለሚመለከተው አካል ቢቀርብም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ተመልካች ሳያገኝ መቆየቱን ተናግረዋል ።

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ብዙ መሻሻሎች እየታዩ ስለሆነ የህዝቡ ቅሬታ በቅርቡ እልባት ያገኛል የሚል ተስፋ እንዳላቸውም የስራ ሒደት ባለቤቱ ገልፀዋል ።

የኢዜአ ሪፖርተር በቦታው በተንቀሳቀሰበት ወቅት እንደታዘበው የመስኖ ልማቱ ተገቢውን አገልግሎት እንዳይሰጥ ያደረጉት የተለያዩ ውስብስብ ችግሮች የተጋረጡበት መሆኑን ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም