የቦታ ጥበት የሚሰጠውን አገልግሎት እያስተጓጎለበት ነው…የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል

62
አዲስ አበባ ግንቦት 28/2010 የተለያዩ አዳዲስ የህክምና አይነቶችን እየሰጠ የሚገኘው የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በቦታ ጥበት የተነሳ የሚጠበቅበትን አገልግሎት መስጠት እንዳልቻለ አስታወቀ። የኩላሊት፣ የህጻናት፣ የውስጥ ደዌ፣ የማህጸንና ጽንስ፣ የአእምሮ፣ የድንገተኛ፣ የቆዳ፣ የአጥንትና የነርቭ ህክምናዎች በሆስፒታሉ ከሚሰጡ አገልግሎቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ። ሆስፒታሉ ህንጻ በመከራየት የህክምና አገልግሎት መስጠቱ ለከፍተኛ ወጪ እየዳረገው እንደሆነም አስታውቋል። የሆስፒታሉ የህክምና ዘርፍ ምክትል ፕሮቮስት ዶክተር ብርሃኔ ረዳኢ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሆስፒታሉ የአገልግሎት አድማሱን በማስፋቱ ከፍተኛ የሆነ መጨናነቅ አለ። የሪፈራል አሰራር የሆስፒታሉን የመቀበል አቅም ከግምት ውስጥ የማያስገባ በመሆኑ ጫና እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑን የሚገልጹት ዶክተር ብርሃኔ የሆስፒታሉን አገልግሎት የሚሹ ታካሚዎች ለአላስፈላጊ እንግልትና ለተጨማሪ የጤና እክል እንደሚዳረጉ ጠቅሰዋል። በቦታ ጥበት ምክንያት ታካሚዎችን ወደ ሌላ የህክምና ተቋም ለመላክ እየተገደዱ መሆኑን ያመለከቱት ኃላፊው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከ800 በላይ ታካሚዎችን ወደሌላ የህክምና ተቋም መላካቸውን አክለዋል። ችግሩንም በጊዜያዊነት ለመፍታት አራት ህንጻዎችን መከራየት ቢቻልም ህንጻዎቹ ለህክምና አገልግሎቱ ምቹ ካለመሆናቸው ባሻገር ለከፍተኛ ወጪ እየዳረጓቸው መሆኑን ገልጸዋል። እንደ ዶክተር ብርሃኔ ገለጻ፤ ሆስፒታሉ የማስፋፊያ ቦታ ጥያቄውን ለሚመለከተው አካል በማቅረብ ግንባታውን ለመጀመር አስፈላጊውን ዝግጅት ቢያጠናቅቅም ግንባታውን ለማካሄድ የሚያስችል ቦታ ለማግኘት ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ አልተሰጠውም። የሆስፒታሉ የህክምና ባለሙያዎች በበኩላቸው በቂ የህክምና አገልግሎት መስጫ ማእከላት ባለመኖራቸው በሚፈለገው ደረጃ አገልገሎት እንዳይሰጡ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ። በዚህም የሚመለከተው አካል የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ጥያቄው ፈጣን ምላሽ እንዲያገኝ ጠይቀዋል። የህክምና አገልግሎት ፈላጊዎች በበኩላቸው የቦታ ጥበቱ የአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ጫና ከማሳደሩም በላይ ለአላስፈላጊ እንግልት እየዳረጋቸው መሆኑን ይገልጻሉ። ኢዜአ የማስፋፊያ ቦታውን አስመልክቶ ጉዳዩ የሚመለከተው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የመሬት ባንክና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎችና ባለሙያዎችን ለማነጋገር በተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም አልተሳካም። በመሆኑም የሆስፒታሉ የማስፋፊያ ቦታ ጥያቄ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ አልተቻለም።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም