የኦሮሞና የሶማሌ ህዝብ ዋነኛው ጥያቄ የሁሉ ነገር መሰረት የሆነው ነጻነትና እኩልነት ነው - የክልሎቹ ርእሳነ መስተዳድሮች

70

ሚያዝያ 23/2011 'የኦሮሞና የሶማሌ ህዝብ ዋነኛው ጥያቄ የሁሉ ነገር መሰረት የሆነው ነጻነትና እኩልነት ነው' ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።

የኦሮሞና የሶማሌ ህዝቦች የወንድማማችነት የሰላም ኮንፍረንስ በአዳማ ከተማ ገልመ አባ ገዳ አዳራሽ እየተካሄደ ነው። 

በኮንፍረንሱ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የሁለቱ ክልሎች ርእሳነ መስተዳድሮች የኦሮሞና ሶማሌ ህዝቦች ድንበር ለሌለው ነጻነትና እኩልነት አብረው የተዋደቁ ወንድማማች ህዝቦች መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በንግግራቸው''ለነጻነት እና እኩልነት ዋና ማሰሪያው ወንድማማችነት ነው፤ ወንድማማችነትን አጠናክሮ በማስቀጠል የላቀች አገር ለመመስረት ሁለቱ ህዝቦች መስዋዕትነት ከፍለዋል'' ብለዋል።

ትናንት ሁለቱን ህዝቦች ለመለያያት ሲሸረብ የነበረውን ሴራ በጣጥሰው አንድነታቸውን ለመገንባት የትናንትናውን ስህተት በይቅርታ መሻራቸውን አብስረዋል።

'የህዝቦች አንድነት ከሴራ በላይ ነው' ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ የትኛውም ሴራ የህዝቦችን አንድነት ሊለያይ እንደማይችል ተናግረዋል።

የሰላም ኮንፈረንስ መድረኩ የኢትዮጵያን አንድነት የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑን የተናገሩት አቶ ሽመልስ፤ እኩይና ክፉ አሳቢዎች እንደሚፈልጉትና እንደሚያስቡት ህዝቡ የሚገፋፋ ሳይሆን አንድነቱን አጠናክሮ የሚቀጥል እንደሆነ ገልጸዋል።

"ኦሮሙማ (ኦሮሞነት) ማቀፍ፣ ነው ሁሉን እንደ አንድ ማየት ነው፣ ከራስ በላይ ለሌላውም መስጠት ነው፣ በመሆኑም ይህንን መልካም ባህል አጎልብተን አንድነቷ የተጠናከረ አገር እንገነባለን'' ብለዋል።

''የኦሮሞነት ቱባ ባህል የሆነው አቃፊነት በአፈናቃዮች አይጨናገፍም'' ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ የኦሮሞና የሶማሌ ህዝብ ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ የበለጠ እንዲጠናከር በህዝብ ለህዝብ አንድነት ላይ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

ለሶማሌ ህዝብ ልዑክ የሰላም ኮንፍረንሱ ወደሚካሄድበት አዳማ ከተማ ድረስ እስኪደርስ በየከተማው የደመቀ አቀባበል ላደረገው ህዝብ ምስጋና አቅርበው ባህሉን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

''ከዚህ በፊት ኦሮ-ቤኒሻንጉልን፣ ኦሮ-አማራን አካሄደናል፤ ቀጥሎ ደግሞ ኦሮ-አፋር፣ ኦሮ-ትግራይና ኦሮ ደቡብን አጠናክረን እንቀጥላለን'' ብለዋል።

ኢትዮጵያን ለማፈራረስ በሚመኙ ሃይሎች እየተካሄደ ያለውን የስም ማጥፋት ዘመቻ ለማምከን ከብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በጋራና በማቀፍ መንፈስ እንደሚሰራ ተናግዋል።

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ በበኩላቸው ''የኦሮሞና የሶማሌ ህዝቦች አንድ ቋንቋ፣ አንድ ባህልና አንድ ደም ያለን ህዝቦች በመሆናችን መቼም አንለያይም፣ አንድነት ኃይል ነው'' ብለዋል።

ለተደረገላቸው ወንድማዊ አቀባበል ልባዊ ምስጋና ያቀረቡት አቶ ሙስጠፌ፤ ህዝቡ በማህበረ ኢኮኖሚያዊና በትግል ትስስሩ የኖረና

ሁለቱ ህዝቦች ሲደርስባቸው የነበረውን ጭቆና በመጋፈጥ ላይ የበለጠ የተሳሰሩ ህዝቦች መሆናቸውን ተናግረዋል።

''በተለይ ለነጻነታቸው ሲያደርጉ የነበረው ትግል ያስተሳሰራቸው፣ ኦሮሞና ሶማሌ ጎረቤት ክልሎች ብቻ አይደሉም አንዱ የአንዱ ቤትም ጭምር ነው'' ብለዋል።

''የህዝቦቹ አንድነት ለኢትዮጵያና ለምስራቅ አፍሪካም ጭምር ኃይል ነው'' ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ከአሁን በኋላ የሁለቱን ህዝቦች አንድነት የሚያናጋ ምንም ኃይል እንደማይኖር ተናግረዋል።

''ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስራቸውን አጠናክረው ወሰናቸውን ለንግድ ክፍት አድርገው አብረው ሰርተው አብረው ነግደው አብረው መልማት አለባቸው'' ብለዋል።

ዛሬ የሚቀመጠው የህዝቦች አንድነት መሰረተ ድንጋይ የኢትዮጵያን ዕድገትና አብሮ መስራት ማስቀጠል የሚቻልበት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።

የኦሮሞና ሶማሌ ህዝቦች አለመጋጨታቸውን የተናገሩት አቶ ሙስጠፌ፤ 'ተጋጭተዋል' ተብሎ የሚነገረው ስህተት መሆኑን አስረድተዋል።

ለዘመናት ከፍተኛ ጭቆና ሲደርስበት የነበረው የኦሮሞ ህዝብ የለውጥ አመራር አግኝቶ ትግሉን ሲያጠናክር ያንን ለማጨናገፍ በምስራቁ በኩል የተሰራበት ሴራ ነው የህዝቦችን መፈናቀልና መገደል ያስከተለው በማለትም የግጭቱ መንስዔ ሴራ መሆኑን ተናግረዋል።

''ወደፊት ይህ ዓይነቱ እንዳይመጣና የተፈናቀሉ ወንድም ህዝቦች ወደ ክልላችን መጥተው ቤታቸው ተመልሰው እንዲኖሩ ቃል እንገባለን'' በማለትም ተናግረዋል።

የፖለቲካ አሻጥር ተወግዶ የጋራ ብልጽግናን እውን እንደሚሆን ያስረዱ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ''ትውልዴ ሐረር በመሆኑ የኦሮሞን ህዝብ ስነ ልቦና አውቃለሁ፤ እንደ ዛሬው ሁለቱን ህዝቦች አንድነትና ደስታን ከማየት በላይ የአእምሮ ረፍት የሚሰጥ የለም'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም