ባለፉት 9 ወራት ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ምርቶች የወጪ ንግድ 103 ሚሊዮን ዶላር ተገኘ

169

ሚያዝያ 22/2011  ባለፉት 9 ወራት ከኢንዱስትሪ ፓርኮች በተገኙ ምርቶች የወጪ ንግድ 103 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ።

አፈጻጸሙ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 40 በመቶ ጭማሪ አለው ተብሏል።

ኮሚሽነር አበበ አበባየሁ ለኢዜአ እንደተናገሩት በበጀት አመቱ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ለማግኘት ከታቀደውም 70 በመቶ ማሳካት ተችሏል።

ጫማና ሌሎች የቆዳ ውጤቶች፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ደግሞ ወደ አውሮፓ፣ አሜሪካ፣ ኤሲያና ሌሎች የገበያ መዳረሻ አገራት የተላኩ መሆናችውንም ተናግረዋል።

 አፈጻጸሙ  ባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ከ73 ሚሊዮን 153 ሺህ ዶላር በላይ የነበረ ሲሆን የዚህ አመት አፈጻጸም የ40 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ገልጸዋል ኮሚሽነሩ።

በስራ እድል ፈጠራ በኩልም በተለያየ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከ70 ሺህ በላይ ሰራተኞች የተቀጠሩ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ባለፉት 9 ወራት 16 ሺህ የስራ እድል መፈጠሩን ገልጸዋል።

ኮሚሽነሩ አክለውም በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች "ሊቆጠር በሚችል መልኩ ጎድቶታል ልንል አንችልም " ሲሉ በኢንቨስትመንት ላይ የጎላ ተጽእኖ አለማድረሱን ነው የተናገሩት።

በዚህ በዘጠኝ ወራት ታዲያ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ መቻሉን ነው የገለጹት።

በተጨማሪም ሰላምና መረጋጋት ያለመኖርም በኢንቨስትመንት ላይ ጫና እንዳያሳድርም ኢንቨስትመንት ቦታዎች ልዩ ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑን አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ ከቅርብ አመታት ወዲህ የወጪ ንግድን ለማሳደግ ታስቦ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ላይ ትኩረት ተደርጓል።

በተጠናቀቁ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የውጭ ባለሃብቶች ለመግባት ስምምነት ቢያደርጉም በሃይልና ሌሎች መሰረተ ልማት አቅርቦት ችግሮች ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ያልገቡ መኖራችውን ገልጸው በቀጣይ ከሚመለከታቸው ጋር ችግሩን በመፍታት ስራ የሚጀምሩ ይሆናልም ብለዋል።

በአሁኑ ሰአት ቦሌ ለሚ ፣ መቀሌ ፣ አዳማ ፣ በተወሰነ ደረጃ ወደ ስራ ገብተዋል በተለይም አዋሳ ኢንዱሰትሪ ፓርክ ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ የገባ ሲሆን በቀጣይ ሌሎች ሲጀምሩ የውጭ ንግድ አፈጻጸም የተሻለ እንደሚሆን ይጠበቃልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ አፈጻጸም ካለፉት አራት አመታት ወዲህ አፈጻጸሙ ቅናሽ እያሳየ መምጣቱን በየአመቱ የሚወጡ ሪፖርቶች ያሳያሉ።

በመሆኑም ከቅርብ አመታት ወዲህ የወጪ ንግድን ለማሳደግ ታስቦ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ላይ ትኩረት የተደረገ ሲሆን ቁጥራቸውን 30 ለማድረስም እየተሰራ መሆኑን የኮሚሽኑ መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም