አብረሃ ወአፅበሃ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና አካባቢ ልማት ላይ ያስመዘገበው ውጤት በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው--- ዶክተር ገመዶ ዳሌ

89
መቀሌ ግንቦት 28/2010 በትግራይ ምስራቃዊ ዞን  የአብረሃ ወአፅበሃ  ቀበሌ  ገበሬ ማህበር  በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት  ላይ ያስመዘገበው ውጤት በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን የአካባቢ ደን ልማትና አየር ንብረት ሚኒስትር ዶክተር ገመዶ ዳሌ ገለጹ። "አካባቢያችንን ከፕላስቲክ ብክለት እንከላከል" በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ የአለም የአካባቢ ቀን  ለ25ኛ ጊዜ  በመቀሌ እየተከበረ ነው። በዓሉን ምክንያት በማድረግ የፌደራል እና የክልል ስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች  የአብረ ወአጽበሃ ቀበሌ ገበሬ ማህበር በጎበኙበት ወቅት ሚኒስትሩ እንዳሉት  ህዝብና አመራሩ ተግባብተውና ተቀናጅተው ከሰሩ ውጤታማ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ ለዚህም  ማሳያው የአብረሀ ወአጽበሃ ቀበሌ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት ባለፉት ዓመታት  ያስመዘገበው ውጤት እንደሆነና ይህም በምሳሌነት እንደሚጠቀስ ተናግረዋል፡፡ በዚህም  አካባቢውን ከወዳደቁ  ፕላስቲክ ነፃ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ዳግም ተምሳሌትነቱን ማሳየት እንደሚገባም አመልክተዋል። "በተፈጥሮ ሀብት ላይ በምንሰራቸው ስራዎችና የሚገኙ ውጤቶች የብዙዎች ቀልብ መሳብ እንደሚቻል ቀበሌው አንዱ ማሳያችን ነው "ብለዋል ሚኒስትሩ። ከሚኒስቴሩ የዘርፉ ባለሙያዎች መካከል   ወይዘሮ አበባ መጫ  በበኩላቸው ፖሊሲና ስትራቴጂ በአግባቡ ወደ  መሬት በማውረድና ቴክኖሎጂን አሟጦ በመጠቀም ለውጤት እንደሚያበቃ  ከቀበሌው መገንዘባቸውን ተናግረዋል። በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ  ስራ እየታየ ያለው ለውጥ የአየርና ለአከባቢ ብክለት መከላከል ያለው  ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ  ከትራንስፖርት ሚኒስቴር የተወከሉና የጉብኝቱ ተሳታፊ  አቶ ጆቢር አያሌው ናቸው። የአብረሃ ወአፅበሃ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አልማዝ  ገብረእግዚአብሔር በሰጡት አስተያየት  ህዝቡና አመራሩ በተፈጥሪ ሀብት ጥበቃና ልማት ለዓመታት ሳይታክቱ በመስራታቸው  አሁን ለተገኘው  ለውጥ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል። የቀበሌው ሊቀመንበር አቶ ገብረሚካኤል ግደይ በበኩላቸው የተፈጥሮ ሃብት ስራ የሁሉም  መሰረት በመሆኑ ህዝብና የቀበለው አስተዳደር ሳያቋርጡ  በመስራታቸው ውጤታማ እንደሆኑ ተናግረዋል። ለዓመታት የዘለቀ  የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ አካባቢው  በድርቅ ከመጎዳት መከላከል መቻሉንም ጠቁመዋል። "ልጆቻችን ሳይሆኑ እራሳችን ውጤት ማየት ጀምረናል" ያሉት ሊቀመንበሩ  የአከባቢው ስነ ምህዳር ከመቀየሩ በተጨማሪ ለእንስሳትና ንብ እርባታ  ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረላቸውን አመልክተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም