የመስኖ ልማት ኑሯቸውን ለማሻሻል እንደረዳቸው በምስራቅ ጎጃም አርሶ አደሮች ተናገሩ

69
ደብረማርቆስ ግንቦት 28/2010 የመስኖ ልማት የገቢ ምንጭ በመሆን ኑሯቸውን ለማሻሻል እንደረዳቸው በምስራቅ ጎጃም ዞን ማቻከልና  ጎዛምን ወረዳዎች አስተያየታቸውን የሰጡ  አርሶ አደሮች ተናገሩ ፡፡ በዘንደሮ የበጋ ወራት በዞኑ በመስኖ ከለማው መሬት 16 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ምርት ተሰብስቧል፡፡ አርሶ አደር ዘገየ ሁነኛው በማቻከል ወረዳ የውላ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ ወራጅ ወንዝና  ምንጭ  በደጃቸው ያለጥቅም እየፈሰሰ የመስኖ ልማት ተጠቃሚ ሳይሆኑ ለዓመታት ሲቸገሩ እንደቆዩ ለኢዜአ ገልጸዋል። ከአምስት ዓመታት ወዲህ በደጃቸው ያለጥቅም የሚፈሰውን ወንዝ በመጥለፍ ሩብ ሄክታር መሬታቸውን  በተለያዩ የጓሮ አትክልቶች በማልማትም ከምርቱ ሽያጭ በዓመት ከ40ሺህ ብር በላይ ገቢ እንደሚያገኙ ተናግረዋል። አርሶ አደሩ እንዳሉት በመስኖ ልማት መሳተፍ ከመጀመራቸው በፊት ኑሯቸው ከእጅ ወደአፍ ነበር፤ የውሃ አማራጮችን ተጠቅመው በበጋው  ወቅት እስከ ሁለት ጊዜ አልምተው ከሚያገኙት ገቢ እስከ 25ሺህ ብር እየቆጠቡ ነው። የመስኖ ልማት ተጠቃሚ መሆን ከጀመሩ ሶስት ዓመት እንደሆናቸው የተናገሩት ደግሞ በጎዛምን ወረዳ የደሳ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ጥላሁን አለሙ ናቸው። "  በበጋ ወቅት ባለኝ ግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ድንች፣ ጥቅል ጎመን፣ ቲማቲምና ለእሸት የሚሆን በቆሎ አመርታለሁ"ብለዋል፡፡ ምርቱንም ለገበያ በማቅረብ በየዓመቱ ከወጪ ቀሪ ከ30 ሺህ ብር በላይ ገቢ እያገኙ ተጠቃሚ መሆናቸውን አርሶ አደሩ ገልጸዋል። የዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር ዋሌ ይርሳው በበኩላቸው ዝናብን ሳይጠብቁ በመስኖ በማልማት የምግብ ክፍተታቸውን መሙላት ከጀመሩ ሰባት አመት እንደሆናቸው  አስታውሰዋል። በመስኖ ልማት መጠቀም ከመጀመራቸው በፊት የዝናብ ወቅትን ጠብቀው እያለሙ በሚያገኙት አነስተኛ ምርት ቤተሰባቸውን ለመቀለብም ሆነ ልጆቻቸውን ለማስተማርም ይቸገሩ እንደነበር ጠቁመዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ግማሽ ሄክታር በማይሞላ ማሳቸው ላይ ገበያ ተኮር የሆኑ የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን በመስኖ አልምተው ለገበያ በማቅረብ  በአንድ የምርት ወቅት እስከ  50ሺህ ብር ገቢ እያገኙ መሆናቸውንም ተናግረዋል። የመስኖ ልማት የገቢ ምንጭ በመሆን ኑሯቸውን ለማሻሻል ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የተናገሩት ፡፡ የዞኑ ግብርና መምሪያ የመስኖ ልማት ባለሙያ አቶ ቀኘ ገዜ እንደገለጹት በዘንድሮ የበጋ ወራት በመስኖ ከለማው  122ሺህ ሄክታር  መሬት መሬት 16 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ  ምርት ተሰብስቧል በቆሎ፣  ቅመማቅመም፣ አትክልትና  የስራስር ሰብል ከተሰበሰበው የምርት ዓይነት ውስጥ ይገኙበታል፡፡ በልማቱም የተሳተፉ  ከ280 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የተለያዩ የውሃ  አማራጮችን ተጠቅመው  በማልማት ከዝናብ ጠባቂነት ተላቀው ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ለመስኖ ልማቱም ከ82ሺህ ኩንታል በላይ የማዳበሪያና የምርጥ ዘር  ጥቅም ላይ መዋሉን ከባለሙያው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም