ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው ሆስፒታል አገልግሎት መስጠት አልጀመረም

ሶዶ ሚያዝያ 21 / 2011 በወላይታ ዞን ገሱባ ከተማ ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ግንባታው ከተጠናቀቀ ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረው የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አገልግሎት መስጠት አልጀመረም፡፡

የከተማው  ነዋሪዎች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት የጤና አገልግሎትን ለኅብረተሰቡ በቅርበት ለማዳረስ ተብሎ የተገነባው ሆስፒታል ያለ አገልግሎት መቀመጠ ተገቢ አይደለም።

መንግሥት ህዝብን ማዕከል ያደረገ የጤና አገልግሎት ለማቅረብ ያስገነባው ህንጻ ያለ አገልግሎት መቆሙ የአገር ሃብትን ለብክነት ዳርጓል ብለዋል፡፡

የከተማ የ01 ቀበሌ ነዋሪው አቶ ማቴዎስ ታንቱ የሆስፒታሉ ግንባታ ተጠናቆ ርክክብ ሲደረግ ፈጥነው ግብዓቶች ተሟልተው ሥራ እንዲጀምር አስታውሼ ነበር ይላሉ።

ሆኖም ማሳሰቢያቸው ሰሚ  አጥቶ እስካሁን አገልግሎት ባለመጀመሩ ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

አቶ አሳምነው አርዮ ለሆስፒታሉ የተቀጠሩ የድንገተኛ ቀዶ ህክምና ከተቀጠሩ አምስት ባለሙያ ናቸው።

እሳቸውን ጨምሮ ሌሎች ባለሙያዎች ሆስፒታሉ ሥራ ባለመጀመሩ ለጊዜው በገሱባ ጤና ጣቢያ እየሰሩ ቢሆንም፤ በሆስፒታል ደረጃ መሰጠት የነበረበትን አገልግሎት ባለመስጠታቸው ሙያውን እንደባከነ እቆጥራለሁ ብለው ይቆጫሉ፡፡

የኅብረተሰቡን የጤና ችግር በቅርበት ይፈታል የተባለለት ሆስፒታል አገልግሎት ባለመስጠቱ ታካሚዎች ወደሌላ ቦታ እየተላኩ ላለአስፈላጊ ወጪና እንግልት እየተዳረጉ ነው ብለዋል፡፡

የገሱባ ከተማ አስተዳደር ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጸጋው ፋንታ ሆስፒታሉ ከ100 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ነዋሪዎች እንዲያገለግል በደቡብ ክልል መንግሥት ተገንብቶ ርክክብ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ ለሆስፒታሉ ግብዓቶች ባለመሟላታቸው አገልግሎት መስጠት እንዳልቻለ ተናግረዋል፡፡

ግንባታዉ እየተጠናቀቀ ሲመጣ የሰው ኃይል ቅጥር መካሄዱን ኃላፊው አመልክተዋል።

ሆስፒታሉ ሥራ ባለመጀመሩ በሕዝብ ዘንድ ቅሬታ መፍጠሩንና የሃብት ብክነት ማስከተሉንም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

በወላይታ ዞን ጤና መምሪያ የህክምና አገልግሎቶች ዋና የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ከበደ ሂዶቶ  ሆስፒታሉን አስመልከቶ የቀረበው ቅሬታ ትክክል ነው ብለዋል፡፡

መምሪያው ሆስፒታሉን በሰው ኃይል ማደራጀቱንም ይናገራሉ።

ለክልሉ ጤና ቢሮ ሆስፒታሉ ስራ የሚጀምርበት ሁኔታ እንዲፈጥር በአካልና በደብዳቤ በተደጋጋሚ ቢያሳዉቁም፤ ምላሹ መዘግየቱን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ ጤና ቢሮ የህክምና አገልግሎት ሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ዮሐንስ ለተሞ  ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ሆስፒታሉ በክልሉ በ2008 ግንባታቸው ከተጀመሩ 21 ሆስፒታሎች ግንባታውን በቅድሚያ መጠናቀቁን አመልክተዋል፡፡

የመድኃኒት ፈንድ አቅርቦት ኤጄንሲ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች እንዲሟሉ እየተጠባበቅን ነው ብለዋል፡፡

ሆስፒታሉን  እስከ 2012 መጀመሪያ ድረስ ሙሉ በሙሉ ስራ ለማስጀመር ታቅዷል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም