ከኒው ዊንግ ቆዳ ፋብሪካ የሚለቀቅ ፍሳሽ ጤናቸውን ማወኩን የሳሪስ አካባቢ ነዋሪዎች ገለጹ

146
አዲስ አበባ ግንቦት 28/2010 በአዲስ አበባ ሳሪስ አካባቢ ከሚገኘው ኒው ዊንግ ቆዳ ፋብሪካ የሚለቀቅ ፍሳሽ ቆሻሻ ጤናቸውን ማወኩን ነዋሪዎች ገለፁ። ፋብሪካው በበኩሉ ዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገጃ ግንባታዬን በማጠናቀቅ ላይ ነኝ ማሽኖችን ከውጪ በማስገባት ላይ መሆኑን አስታውቋል። በመዲናዋ ከሚገኙት ሰባት የቆዳ ፋብሪካዎች መካከል ስድስቱ በፍሳሽ አያያዝና አወጋገድ ስርዓት አካባቢን እየበከሉ በመሆኑ ከሰባት ወራት በፊት በአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ትእዛዝ ታሽገው ነበር። ሆኖም ተቋማቱ ለሀገር ያላቸውን ሚና ግምት ውስጥ በማስገባት በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ የሚስተዋልባቸውን ችግር በማስተካከል ለውጥ ማምጣት ካልቻሉ በድጋሚ ሙሉ በሙሉ እንደሚታሸጉ በማስጠንቀቅ እሸጋው እንዲነሳላቸው ተወስኖላቸው ነበር። የተሰጠው የጊዜ ገደብ ባለፈው ሚያዚያ 30 ቀን 2010 ዓ.ም የጠናቀቀ ቢሆንም ፋብሪካዎቹ አሁንም አካባቢ መበከላቸውን ባደረግነው ምልከታ አረጋግጠናል። በሳሪስ የሚገኘው ኒው ዊንግ ቆዳ ፋብሪካ ከነዚህ መካከል አንዱ ሲሆን ሁኔታው አሁንም ድረስ የጤና ጠንቅነቱ መቀጠሉን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል። የኒው ዊንግ ቆዳ ፋብሪካ  አሰራራቸውን እንዲያሻሽሉ ቀነ ገደብ ከተሰጣቸው ፋብሪካዎች መካከል አንዱ ነው፤ ሆኖም ነዋሪዎች እንደሚሉት ፋብሪካው አሁንም ለአካባቢው ብክለትና የሰዎች ጤና ጠንቅ መንስኤነቱ አንደቀጠለ ነው። ነዋሪዎቹ በሰጡት አስተያየት ለህይወታቸው አደጋ እየሆነ የመጣውን ችግር እንዲወገድላቸው የሚመለከታቸውን አካላት ሁሉ ለማነጋገር ቢሞክሩም መፍትሄ አላገኙም፤ የሚሰጣቸው ምላሽ "ይጣራል፤ ታገሱ" ከሚሉ ቃላት ውጭ የዘለለ አለመሆኑን ተናግረዋል። ለልማት ሲባል የሰው ልጅ መጎዳት የለበትም፤ በማለትም መንግስት ተገቢውን መፍትሄ እንዲሰጣቸው መፍትሄ ነው ያሉትን  ጠቁመዋል። የኒው ዊንግ ቆዳ ፋብሪካ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢቫኖ መስፍን እንዳሉት በአሁኑ ወቅት የፍሳሽ  አወጋገድ ስርዓቱን ለማጠናከር የተካሄደው ግንባታ ቢጠናቀቅም አስፈላጊ መሳሪያዎችን ከውጪ የማስመጣቱን ሂደት በተሰጠው የስድስት ወራት የጊዜ ገደብ ማጠናቀቅ አልተቻለም። ምክትል ሥራ አስኪያጁ አክለውም የተለያዩ ኬሚካሎችን በመጠቀም ከፋብሪካው ይወጣ የነበረው መጥፎ ሽታ እንዲቀንስ ተደርጓል ብለዋል። በመጪዎቹ ሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ችግሩን ሙሉ ለሙሉ ለማስወገድ ጥረት እንደሚደረግም ገልፀዋል። የባለስልጣኑ ስራ አስኪያጅ አቶ ፀጋዬ ገብረማርያም  እንደሚሉት ሁሉም ፋብረካዎች በተሰጣቸው ጊዜ ውስጥ የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት የየራሳቸውን አንቅስቃሴ ያደረጉ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ማጠናቀቅ ግን አልቻሉም። የተሰጠው ጊዜ መጠናቀቁን ተከትሎ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እስከ መስከረም ድረስ ተጨማሪ የማጠናቀቂያ ጊዜ እንዲሰጣቸው ተጠይቋል ያሉት ሥራ አስኪያጁ ተጨማሪ ጊዜው የተጠየቀበት ምክንያት ማሽነሪዎችን ለማስገባት የዶላር እጥረት አለ በሚል ነው ብለዋል። የከተማ አስተዳደሩ ይህንን በማጤን ባለስልጣኑ ከአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ጋር ጥናት አድርጎ የውሳኔ ሃሳብ እንዲያቀርብ ቀነ ቀጠሮ መያዙም ተመልክቷል። ሆኖም በዶላር ሳቢያ በሰውና በእንስሳት ህይወት ላይ ችግር መፈጠር እንደሌለበትም ገልፀዋል። ለፋብሪካዎቹ ተጨማሪው ጊዜ ተሰጥቶ የሚፈለገውን ለውጥ ካላመጡ ግን ባለስልጣኑ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወሰድ ስራ አስኪያጁ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ችግር እንዳለባቸው በማረጋገጥ ባለፈው ጥቅምት 2010 አሽጓቸው የነበሩት ሌሎቹ የቆዳ ፋብሪካዎች ድሬ፣ አዲስ አበባ፣ አዋሽ፣ ባቱና ዋልያ በሚል የሚጠሩት ናቸው።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም