የአገሪቷ የለውጥ እንቅስቃሴ ዜጎች ሃሳባቸውን በነፃነት እንዲገልጹ አስችሏል-የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች

69

ሚያዝያ 19/2011በኢትዮጵያ ባለፈው አንድ ዓመት የተደረገው የለውጥ እንቅስቃሴ ዜጎች ሃሳባቸውን በነፃነት የመግለፅ መብታቸውን እንዲጠቀሙ ያስቻለ ነው ሲሉ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ገለጹ፡፡

በ1966/67 እና የ1983 ዓ.ም የለውጥ ጊዜያት በአንፃራዊነት ጋዜጠኛው እንደልቡ የፃፈባቸው ጥቂት አጋጣሚዎች ነበሩ ይላሉ አስተያየት ሰጪዎቹ።

ባለሙያዎቹ ይህንን ያሉት የፕሬስ ቀንን ምክንያት በማድረግ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጡት አስተያየት ነው፡፡

የዘንድሮው 20ኛው የዓለም የፕሬስ ቀን  ሚያዝያ 23 ቀን 2011ዓ.ም በኢትዮጵያ ይከበራል።

የዘርፉ ባለሙያዎች ደግሞ በዓሉ በአገሪቷ የመከበሩ ምስጢር መሠረታዊ የሆኑ ለውጦች መካሄዳቸውና የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ማሻሻያ ፕሮግራሞች በመከናወናቸው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ይኽው ጅማሬ ሳይስተጓጎል እንዲቀጥልም ይመክራሉ ባለሙያዎቹ፡፡

ባለፈው አንድ ዓመት በአንፃራዊነት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ነጻ የሚዲያ ድባብ አለ ያሉት የፎርቹን ጋዜጣ የትምህርትና የስልጠና ክፍል ኃላፊ አቶ ጥበቡ በቀለ ናቸው፡፡

ይሁንና ህጎች በመቀየር ላይ እንዳሉና እየተረቀቁ መሆኑን ጠቁመው በህግ ደረጃ ግን እስካሁን የተቀየረ ነገር አለመኖሩን አልሸሸጉም።

ነገር ግን ከከፍተኛ አመራሮች ጀምሮ ከሚነገረው ነገር በመነሳት ነፃነት ያለበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው ማለት ይቻላል ብለዋል።

ወደፊት እየተረቀቀ ያለው ህግ ነፃነትን የሚጠብቅና የጋዜጠኛውን መብት የሚያስጠብቅ ብሎም ጥሩ የሚዲያ ነፃነት ያለበት ሕግ ሆኖ እንደሚወጣ እንጠብቃለንም ብለዋል፡

የፕሬስ ነፃነት ማለት የሕዝብ የማወቅ መብት ነው፤ የፕሬስ ነፃነት ሲባል ለጋዜጠኞች መሟገት አድርጎ የሚያስብ ቢኖርም፤ የፕሬስ ነጻነት ማለት ለሕዝብ መሟገት ማለትም ነው ምክንያቱም የማወቅ መብት ያለውና ያንን መብት የተጠቀመ ህዝብ ነው ሊያውቅ የሚችለው ይላሉ ባለሙያዎቹ።

የፕሬስ ነፃነት "ከማሰብ ነፃነት የሚጀምር ነው" ይህም እያንዳንዱ ዜጋ የፈለገውን በነፃነት የማሰብና ያሰበውን የመናገር መብት ሲኖረው ነው ከሚለው ይመነጫል ነው ያሉት ባለሙያዎቹ፡፡

የቀድሞው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ንጉስ ወዳጅነው እንዳሉት አሁን ባለው ሁኔታ የወጡ ህጎች በተገቢው ሁኔታ ለማስፈፀም የሚያስችሉ የሚዲያ ተቋማትን የመፍጠርና ባለሙያውም በዚያ ሥነ ልቦና እንዲቀሳቀስ የማድረግ ሥራ ተጀምሯል፡፡

ሆኖም የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን አሁንም ስኬት ላይ ብቻ የመንጠልጠል ችግር ይታይባቸዋል ብለዋል።

የወጡትን ህጎችም በተገቢው መንገድ ሥራ ላይ ለማዋል ሚዲያው የሕዝብ ድምፅ መሆኑን ማረጋገጥ፣ በመንግሥትና በህዝብ መካከል ድልድይ ሆኖ ማገልገል ፣ ከአድልዎ ነፃ ሆኖ መሥራት፣ ጥላቻን የሚያስፋፉና ግጭትን የሚቀሰቅሱ ነገሮችን ማቆም እንዲሁም ለሀገራዊ ጥቅምና ለጋራ ጉዳይ ትኩረት መስጠት አለባቸው ብለዋል፡፡

በመንግሥት በኩልም በማህበራዊ ሚዲያ አካባቢ ያለውን አሠራር ለማሻሻልና የህግ ማዕቀፍ ለማዘጋጀት የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ መሠረታዊውን የህግ ማዕቀፍ በማይጣረስ መልኩ ተጠያቂነትንና ግልፅነትን በሚያስፈን መልኩ ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት ይገልጻሉ አቶ ንጉሱ።

የፕሬስ ነፃነትን ለማስፋፋት የሚሰራ ነፃና ገለልተኛ አካላት ያሉበት አንድ ብሔራዊ ኮሚቴ ወይንም ኮሚሽን ቢቋቋምና በአንድ ወገን የመገናኛ ብዙሃኑን መብት ለማስከበር ቢሰራ መልካም መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ የቀድሞ የአዲስ ዘመን ዋና አዘጋጅና የጋዜጠኝነት መምህር አቶ ማዕረጉ በዛብህ ናቸው።

በሌላ በኩል ደግሞ ጋዜጠኞች የግለሰብን መብት ከማክበር ጀምሮ በሕግ አግባብ ሥነ ምግባርን ተላብሰው ቢሰሩ የዳበረ የፕሬስ ነፃነት ለመፍጠር ይረዳል ብለዋል።

በመንግሥት በኩል የሚታዩትን ችግሮች በመንቀስ የመፍትሔ አቅጣጫ የሚያመላክቱትን፣ የሕዝብን ድምፅ የሚያሰሙትን፣ የመንግሥትም ሆነ የግል መገናኛ ብዙሃንን ከማፈንና ከማሳደድ ይልቅ ማበረታትና መደገፍ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሕዝቦች በተወካዮቻቸው በኩል ራሳቸውን ያስተዳደራሉ፣ ተወካዮቻቸውን ለመምረጥ ምን እየተከናወነ እንዳለና የተወከለው መንግሥት ምን እየሠራ እንደሆነም ማወቅ አለባቸው ብለዋል።

ይህ የሚከናወነው ደግሞ በመገናኛ ብዙሃን በኩል በመሆኑ መንግስት ለስኬቱ ድጋፉን ማጠናከር አለበት ብለዋል።

የአሐዱ ራዲዮ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ባለፉት 27 ዓመታት ግዙፍ የመንገድ ፣ የግድብና የባቡር መሠረተ ልማቶችን ገንብታለች። ነገር ግን አገሪቷ መገናኛ ብዙሃንን በሚገባው ልክ መገንባት አልቻለችም፤ እንዳውም የተቋቋሙትን በማጥፋትና በማዳከም ነው ያሳለፈችው ብለዋል፡

በዚህ የተነሳ አገሪቷ ጠንካራ መገናኛ ብዙሃን የላትም፤ ወደ 107 ሚሊዮን ለሚጠጋ ህዝብም 10 ሺህ ኮፒ የሚያሳትም ጋዜጣ ስለሌላት ህዝብም በቂ መረጃ ማግኘት አልቻለም ነው ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፡፡

አቶ ጥበቡ እንድሚሉት ደግሞ ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ማስተዳደር ከጀመረ ጊዜ አንስቶ 350 ጋዜጦችና መፅሄቶች ሥራ ጀምረው ነበር፤ እነዚህ ጋዜጦችና መጽሄቶች አሁን ላይ ሁሉም በሚባል ደረጃ መዘጋታቸውን ባደረጉት ጥናት ማረጋገጣቸውንም ጠቅሰዋል።፡

1966/67 ዓ.ም. እና ኢህአዴግ አገሪቷን እንደተቆጣጠረ የቅድመ ሳንሱር ህግ ተነስቶ የግል ሚዲያዎች የተፈቀዱበት ጊዜ በአንፃራዊነት ለቀቅ ተደርጎ ጋዜጠኛው እንደልቡ የፃፈባቸው  ጊዜያት እንደነበሩ የፎርቹን ጋዜጣ የትምህርትና የሥልጠና ክፍል ኃላፊ አቶ ጥበቡ በቀለ ያስታውሳሉ፡፡

አቶ ንጉሱም በአገሪቷ የፕሬስ ነጻነት “ሀ” ብሎ የጀመረው ኢህአዴግ ሥልጣን በተረከበ ማግስት ሲሆን በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 29 ላይ እንደተደነገገው የዜጎች ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት እውቅና አግኝቷል ብለዋል፡፡

 የፕሬስ ነፃነት በአንጻራዊነት በአገሪቱ የተጀመረው በ1983 የመንግሥት ለውጥ ከተደረገ በኋላ መሆኑን የቀድሞው የአዲስ ዘመን ዋና አዘጋጅና የጋዜጠኝነት መምህር አቶ ማዕረጉ በዛብህም ይናገራሉ።

በዚህ ወቅት የግሉ ዘርፍም በስፋት ሚዲያውን የተቀላቀለበት ወቅት እንደነበርና የግል ጋዜጦችና መፅሄቶች መስፋፋትን ተከትሎ ስለ ፕሬስ ነፃነት በስፋት መነገርም መተግበርም ጀምሮ እንደነበር ይገልጻሉ።

የአሐዱ ራዲዮ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ እንዳሉት ደግሞ በ1987 ዓ.ም. የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ፀደቀ፣ የመገኛኛ ብዙሃንም ነፃነትም ታወጀ፣ ነጻነቱ በተገኘ ማግስት የግሉ ፕሬስ በስፋት ተከፈተ።

በወቅቱ በርካታ የመገናኛ ብዙሃን ቢከፈቱም ሳይውል ሳያድር ፈተና ገጠማቸው፤ በወረቀት ላይ ነጻነት ቢፈቀድላቸውም ፤ በተግባር ግን ለመስራት ነጻነት አጡ ይላሉ።

በመገናኛ ብዙሃንና ጋዜጠኞች ላይ አፈና፣ ማሳደድ፣ ወከባ፣ መረጃ መከልከልና ሌሎች በርካታ ጫናዎችም እንደነበሩባቸውም ባለሙያዎቹ አስታውሰው፣ አሁን የተከፈተውን ነጻነት በህግ ማስደገፍና ለዘላቂነቱ መስራት ለአገሪቷ እንደሚበጅ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም