በበዓሉ ሊፈፀሙ የሚችሉ ወንጀሎችን ለመከላከል እየተሰራሰ ነው-የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን

69

ሚያዝያ 18/2011 የትንሳኤ በዓልን ተከትሎ ሊፈፀሙ የሚችሉ የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ሰኢድ አህመድ ለኢዜአ እንደገለጹት በዓሉ በሰላም እንዲከበር ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በቂ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ስራ ተገብቷል ።

"በዓሉን ምክንያት በማድረግ በግልም ሆነ በቡድን ሊፈፀሙ የሚችሉ ወንጀሎችን በመለየት የፀጥታ መዋቅሩ የጋራ እቅድ ይዞ ተሰማርቷል"ብለዋል።

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የእንስሳ ስርቆትና የማታለል ወንጀል ሲፈፅሙም ሆነ ለመፈፀም ሲሉ የተደረሰባቸው ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቅሰዋል ።

በተለይ በከተሞች አካባቢ ለግብይት የሚመጣን ሰው ኪስ በማውለቅና ተከታትለው የስርቆት ወንጀል ሲፈፅሙ እጅ ከፍንጅ የተያዙ መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ወንጀል ፈፅመው የተሰወሩ ላይም ክትትል እየተደረገ ነው።


በበዓሉ ወቅት ሀሰተኛ የብር ኖት ዝውውር በብዛት ሊኖር ስለሚችል ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን የገለፁት ረዳት ኮሚሽነሩ ህብረተሰቡም በግብይት ወቅት ከድርጊቱ እራሱን እንዲጠብቅ አሳስበዋል ።

በበዓላት ወቅት  ህብረተሰቡ ችግር ሲገጥመው በማንኛውም ጊዜና ቦታ በአካባቢው የሚገኝን ፖሊስ እርዳታ እንዲጠይቅም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በተጨማሪም  በስልክ ቁጥር 0582201327 በመደወል የፖሊስን እርዳታ ማግኘት እንደሚቻል ረዳት ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም