በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የትንሳኤ በዓልን በመጠለያዎች ከሚገኙ ተፈናቃዮች ጋር ለማከበር ዝግጅት ተደረገ

206

 ሚያዝያ 18/2011 በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በጊዜያዊ መጠለያዎች የሚገኙ  ከ32ሺ በላይ ተፈናቃዮች ጋር የትንሳኤ በዓልን  በጋራ ለማክበር  ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ፡፡

 የዞኑ አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባባሪያ ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መንበሩ አውደው ለኢዜአ እንደተናገሩት ተፈናቃዮች በዓሉን በአብሮነት ስሜት እንዲያከብሩ የክልልሉ መንግስት ከ420ሺህ ብር በላይ መድቧል፡፡

“በተመደበው ገንዘብ የእርድ እንስሳትን ጨምሮ ምግብና መጠጦችን በማዘጋጀት በዞኑ አራት ጊዚያዊ መጠለያዎች የሚገኙ የሁለቱ ማህበረሰብ ተፈናቃዮች በዓሉን በአብሮነት ስሜት እንዲያከብሩ ይደረጋል” ብለዋል፡፡

የአማራ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት ደግሞ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ከአማራና ቅማንት የተዋለዱ 200 የህብረተሰብ ክፍሎችን በጎንደር ከተማ የአብሮነት የምሳ ግብዣ ዝግጅት ማድረጉንም ኃላፊው አመልክተዋል፡፡

መገናኛ ድርጅቱ የአብሮነት የምሳ ግብዣውን በዕለቱ በቀጥታ ስርጭት ሽፋን ለመስጠት መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል፡፡

 በሌላም በኩል ደግሞ በአሜሪካ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆችም የትንሳኤን በዓል ምክንያት በማድረግ በጎንደር ከተማ 1ሺ የሚሆኑ ተፈናቃዮችን ምሳ ለመጋበዝ  ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በማዕከላዊ  ጎንደር ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ከ59ሺ በላይ አባወራና ቤተሰቦቻቸው በጊዚያዊ መጠለያዎችና ከቤተሰብ ጋር ተጠግተው እንደሚገኙ ቀደም ብሎ ተገልጿል፡፡